አሜሪካውያንን የያዘው የመጨረሻ ወታደራዊ በረራ ከካቡል ተነሳ

የታሊባን ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አሜሪካ ለሁለት አስር ዓመታት በአፍጋኒስታን የነበራትን ቆይታ ማብቃቱን የሚያበስረው የመጨረሻው የሃገሪቱ ወታደራዊ በረራ ከካቡል ተነስቷል።

የአካባቢው የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራል ኬኔት ማኬንዚ እንዳሉት የመጨረሻው የ ሲ17 አውሮፕላን ማክሰኞ ከእኩለ ሌሊት ግድም በኋላ የአሜሪካ አምባሳደር ጭምር አሳፍሮ ከካቡል ወጥቷል።

ቀነ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት መውጣት ያልቻሉትን ለመርዳት የዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮው ይቀጥላል ሲሉም አክለዋል።

የመጨረሻው አውሮፕላን ከሄደ በኋላ በታሊባኖች የደስታ ተኩስ ሲተኮስ ተሰምቷል።

የመጨረሻ አውሮፕላን መውጣት የአሜሪካን ረዥሙ ጦርነት እና ታሊባን ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ነሐሴ 14 ላይ የተጀመረው በርካታ ሰዎችን የማስወጣት ሥራ ማብቃቱን ያመለክታል።

ጄኔራል ማክኬንዚ በአጠቃላይ የአሜሪካ እና የአጋሮቿ አውሮፕላኖች ከ 123 ሺህ በላይ ሲቪሎችን ከሃገሪቱ አስወጥተዋል። በቀን በአማካይ ከ 7ሺህ በላይ ሰዎችን እንደማለት ነው።

ከመጨረሻው በረራ በኋላ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በዋሽንግተን ባደረጉት ንግግር "ግዙፍ ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሰብዓዊ ተግባር" እና አሜሪካ እስካሁን ካከናወኗቸው በጣም ፈታኝ ጉዳዮች አንዱ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

‹ አዲስ ምዕራፍ ተጀምሯል። ወታደራዊ ተልዕኮው አልቋል። አዲስ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ተጀምሯል" ብለዋል።

ታሊባን እውቅና ማግኘት እንዳለበት እና ይህም የሚወሰነው የገባውን ቃል በመጠበቁ እና ግዴታዎቹን በመወጣቱ ነው ብለዋል።

በዚህም ሲቪሎች በነጻነት ወደ ሃገሪቱ እንዲገቡ እና እንዲወጡ፣ ሴቶችን ጨምሮ የሁሉም አፍጋኒስታንን መብቶች በመጠበቅ እና የሽብር ቡድኖችን በመከልከል እንደሚወሰን ተናግረዋል።

አክለውም አሜሪካ በካቡል ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋሟን አቋርጣ ሥራዎችን ወደ ዶሃ አስተላልፋለች ብለዋል።

አሜሪካዊያንን እና የአሜሪካ ፓስፖርት ያላቸው አፍጋኒስታኖችን ሃገሪቱን ለቀው ለመውጣት ከፈለጉ ለመርዳት ለመርዳት "የማያቋርጥ ጥረቷን" ትቀጥላለች ሲሉ ገልጸዋል።

ብሊንከን ስለ ጦሩ መውጣት የተናገሩ የመጀመሪያው የባይደን አስተዳደር ካቢኔ አባል ናቸው።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፉት 17 ቀናት በማስወጣት ሥራው የተሳተፉትን ሁሉ አመሰግነው ማክሰኞ ለሕዝቡ ንግግር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩናይትድ ስቴትስ በአፍጋኒስታን በተጠርጣሪ የአጥፍቶ ጠፊ ላይ ባደረሰችው የድሮን ጥቃት ስድስት ሕፃናትን እና ለአሜሪካ ኃይሎች አስተርጓሚ ሆኖ የሚሠራ ሰውን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን መገደሉን በተመለከት ምንም ማብራሪያ አልሰጠችም።

የሟች ዘመዶች በካቡል አየር ማረፊያ አቅራቢያ ባለ መኪና ላይ ያነጣጠረው ጥቃት በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል። ፔንታጎን ዘገባዎቹን እየመረመረኩ ነው ብሏል።