ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ጤና ድርጅት ለደሃ አገራት ክትባቱ እስኪዳረስ ሶስተኛው የኮቪድ ክትባት እንዲገታ ጠየቀ
የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱን የመከላከለል አቅም መጠን ለመጨመር በሚል የማበረታቻ ወይም ሶስተኛ የኮቪድ-19 ክትባት ቢያንስ እስከ መጪው መስከረም መገባደጃ ድረስ ገታ እንዲደረግ ጠይቋል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም እንዳሉት መሰል እርምጃ ቢያንስ 10 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ህዝብ ክትባቱን እንዲያገኝ ያስችላል።
እንደ እስራኤልና ጀርመን ያሉ አገራት ደግሞ ሶስተኛ የኮቪድ-19 ክትባት ለዜጎቻቸው ለመስጠት ማሰባቸውን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
ነገር ግን ኃላፊው ደሃ የሚባሉት አገራት በክትባት ሂደቱ ወደኋላ እየቀሩ እንደሆነ አሳስበዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ መሰረት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ካለው የክትባት እጥረት አንጻር ለእያንዳንዱ 100 ሰው 1.5 ክትባቶችን ብቻ ማቅረብ እንደሚችሉ ያሳያል።
ዶክተር ቴድሮስ ክትባቶቹ ተመልሰው መሰብሰብ እንዳለባቸውና ከተሰበሰበው ክትባት አብዛኛው ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገራት መሰራጨት እንዳለበት አሳስበዋል።
አክለውም ''ሁሉም መንግስታት ዜጎቻቸውን ከአዲሱ የዴልታ ዝርያ ለመከላከል እያደረጉ ያሉትን ነገር እረዳለሁ። ነገር ግን በዓለማችን ያለውን አብዛኛውን ክትባት የተጠቀሙት አገራት መልሰው አሁንም ክትባቱን እንዲጠቀሙት መፈቀድ የለበትም'' ብለዋል።
ከፍተኛ ገቢ ባላቸውና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት መካከል ያለውን የክትባት ልዩነት ለመቀነስ እየሰራ የሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት የአሁኑ ጥያቄው ከበድ ያለ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
ድርጅቱ በሁሉም አገራት ከሚገኙ ዜጎች መካከል ቢያንስ 10 በመቶ የሚሆኑት እስከሚቀጥለው ወር መጨረሻ ድረስ ክትባቱን እንዲያገኙ እቅድ ያወጣ ቢሆንም ነገሮች አሁን እየሄዱበት ካለው ፍጥነት አንጻር ግን ላይሳካ እንደሚችል ተገምቷል።
እንደ ሄይቲ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ ባሉ አገራት እስካሁን ድረስ ሁለተኛውን ዙር ክትባት የወሰደ ሰው የለም።
ኢንዶኔዢያ ውስጥ ደግሞ ባለፈው ወር እንደ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን አገሪቱ ግን መከተብ የቻለችው 7.9 በመቶ የሚሆነውን ህዝቧን ብቻ ነው።
በሌላ በኩል እስራኤል እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አዋቂዎች ተጨማሪ ክትባት እንዲያገኙ እያሰራጨች ሲሆን ጀርመን ደግሞ ሞደርና እና ፋይዘር ክትባቶችን ለሶስተኛ ዙር ለማሰራጨት ማሰቧን ማክሰⶉ ዕለት አስታውቃለች።
ከዚህ በተጨማሪ በዩናይትድ ኪንግደም ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ ዜጎች ከመጪው ወር ጀምሮ ማጠናከሪያ ክትባቶችን እንደሚያገኙ ተገልጿል።
አሜሪካ እስካሁን የማጠናከሪያ ክትባቶችን በተመለከተ ምንም ያለቸው ነገር ባይኖርም ዋይት ሃውስ ግን ረቡዕ ዕለት አሜሪካውያን በሙሉ እንዲከተቡ የሚያስችልና ለሌሎች አገራት ጭምር የሚላክም ክምችት እንዳለ አስታውቋል።
ዶክተር ቴድሮስ ሀብታም አገራት ክትባቶችን ወደ ድሃ አገራት መላክ እንዲጀምሩ ሲጠይቁ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።
ግንቦት ወር ላይ ሀብታም አገራት ለህጻናትና ለታዳጊዎች ሚሰጡትን ክትባት ቀነስ አድርገው ወደ ደሃ አገራት ክትባቶቹን መላክ እንዲጀምሩ ጠይቀው ነበር።
ኃላፊው ያደጉት አገራት ኮቫክስ በተሰኘው ዓለም አቀፍ ጥምረት በኩል በፍትሀዊነት ክትባቶቹን ለማድረስ እንዲሰሩ ቢጠይቁም እንደ ዩኬ ያሉ በርካታ አገራት ግን ህጻናትና ታዳዊቾን የመከተብ እቅዳቸውን በፍጥነት እየገፉበት ይገኛሉ።