ሙዚቀኛዋ ሪሃና በይፋ የቢሊየነሮችን ጎራ ተቀላቀለች

ታትሟል

ሙዚቀኛዋና ተራማጅ የፋሽን ኢንዱስትሪ ባለድርሻዋ ሪሃና በይፋ የቢሊየነሮች መዝገብ ላይ ስሟ መስፈር ችሏል።

ፎርብስ የተሰኘው የልጥጥ ሃብታሞችን የባንክ ደብተር የሚያወዳድር መፅሔት፤ ሪሃን በዓለማችን ካሉ ቱጃር ሴት ሙዚቀኞች አንዷ ሆናለች ብሏል።

የፖፕ ሙዚቃ ኮከቧ ሪሃና 1.7 ቢሊዮን ዶላር አላት፤ ከዚህ መካከል 1.4 ቢሊዮን ዶላሩ የመጣው ፌንቲ ከሚባለው የመዋቢያ ምርቶች ፈብራኪ ድርጅቷ ነው ብሏል ፎርብስ።

ይህ ዶላር አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ ቢመታ ወደ 76 ቢሊዮን ብር ሊመነዘር ይችላል።

የሪሃና የተቀረ ሃብት የሚመጣው ሳቬጅ ኤክስ ፌንቲ ብላ ከሰየመችው የውስጥ ልብስ መሸጫ ሱቋ ነው።

ከዚህ ከምታገኘው ዶላር በተጨማሪ ከሙዚቃና ከትወና የምታገኘውም የሚናቅ አይደለም ይላል መፅሔቱ።

በመዝናኛው ዓለም ካሉ ልጥጥ ሴቶች ሪሃና ከጉምቱዋ ኦፕራህ ዊንፍሬይ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን ተቆናጣለች።

ሮቢን ፌንቲ በተሰኘ የመዝገብ ስሟ የምትታወቀው ሪሃና፤ ፌንቲ ቢውቲ ስትል የመዋቢያ ምርቶችን መቸብቸብ የጀመረችው በፈረንጆቹ 2017 ነበር።

በወቅቱ የድርጅቴ ዓላማ ለሁሉም ዓይነት ሴቶች የሚሆን ምርት ማምረት ነው ስትል ተናግራ ነበር።

ቃሏን ሳታጥፍም 40 ዓይነት ቀለም ያላቸው 'ፋውንዴሽን ሼድ' የተሰኙ መዋቢያዎችን አምርታ ብዙዎችን አጀብ አስኝታ ነበር።

የፌንቲ ተፅዕኖ ጎልቶ መውጣት የጀመረው ተቀናቃኝ ፋብሪካዎች የሪሃናን ዱካ መከተል ሲጀምሩ ነው።

ሪሃን ኤልቪኤምኤች ከተሰኘው ድርጅት ጋር በጥምረት ያቋቋመችው ፌንቲ በመጀመሪያው ዓመት 550 ሚሊዮን ዶላር ማትረፉ ተነግሯል።

ነገር ግን ሪሃና ሌሎችም ያዋጡኛል ብላ የከፈተቻቸው ነገር ግን መልሳ የዘጋቻቸው ሱቆች አሏት።

የ33 ዓመቷ የሙዚቃ ኮከብና የተመሰከረላት ቱጃር አንድ የፋሽን 'ብራንድ' ነበራት። ነገር ከተከፈተ ሁለት ዓመት ሳይሞላው እንዲዘጋ ሆኗል።

ባርቤዶስ የተወለደችው ሪሃና ከ250 ሚሊዮን በላይ የሙዚቃ ሥራዎቿ ተሸጠውላታል።

ሪሃና አልበም ካወጣች 6 ዓመት ሊሞላት ነው። ለመጨረሻ ጊዜ አልበም የለቀቀችው 2016 ላይ ሲሆን አድናቂዎቿ የአልበም ያለህ እያሉ ይገኛሉ።

ነገር ግን በቅርቡ ከፍቅር ጓደኛዋ ራፐር ኤሳፕ ሮኪ ጋር አንድ የሙዚቃ ቪድዮ ስትቀርፅ በድብቅ ታይታለች።