ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሰብዓዊ በረራ ከየመን ተመለሱ
አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከየመን ባለስልጣናት ጋር በመተባበር 79 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በትናንትናው ዕለት ከየመን መመለሱን አስታውቋል።
በሁለት አመታት ውስጥ የመጀመሪያው ነው በተባለው በዚህ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሰብዓዊ በረራ 19 ሴቶችና 14 ህፃናት መካተታቸውም ተገልጿል።
"አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ይህንን በትብብር የመመለስ ጥረት የዓለም አቀፉን ፕሮቶኮሎችና ደረጃዎችን በተከተለ መልኩ ለመቀጠል ዝግጁ ነው። ከሰንዓ የሚደረገው የመመለስ ስራም እንደሚቀጥልም ተስፋ አድርጋለሁ " በማለት የመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ቀጠናዎች ዳይሬክተር ካርሜላ ጎዴው ተናግረዋል።
በትናንትናው ዕለት የተደረገው በረራም በዓለም ዙሪያ ሁሉንም የብዝበዛ ዓይነቶች ለመዋጋት ዓላማ ካለው የዓለም ፀረ- የህገወጥ ሰዎች ዝውውር ቀን ከተከበረ ከአራት ቀናት በኋላ ነው።
በየመን የሚገኙ ስደተኞች በአስቸጋሪ ሁኔታ ድንበሮችን አቆራርጠው የመጡ ሲሆን በመንገዳቸውም ላይ ለደህንነታቸውና ክብራቸውን አደጋ ውስጥ የሚጥሉ ሁኔታዎችን ይጋፈጣሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በመደበኛነት የህገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችም ኢላማም ይሆናሉ። እንዲሁም አስፈላጊ አገልግሎቶችን እና ድጋፍ ለማግኘትም ብዙ መሰናክሎች ያጋጥሟቸዋል።
የ አይኦኤም በፈቃደኝነት ላይ የተመረኮዘ የሰብዓዊ በረራ መርሃ ግብር ድርጅቱ በአገሪቱ ውስጥ ስደተኞችን የሚረዳበት እና ለተጨማሪ በደል እና ጉዳት ሰለባ እንዳይሆኑ የሚከለክልበት አንዱ መንገድ እንደሆነም ተገልጿል።
"በየመን የሚኖሩ ስደተኞችና ወደ አገራቸው መምጣት የሚፈልጉ ስደተኞች ሁሉ ክብሩን በጠበቀ መልኩና በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ለመመለስ እንዲችሉ ከፍተኛ ጥረት በአስቸኳይ ያስፈልጋል" በማለት በአይኦኤም የኢትዮጵያ ስደተኞች አስተዳደር ክፍል ኃላፊ ማማምቦ ሙንጋ ተናግረዋል
አይኦኤም ከስደት ተመላሾች ለጉዞ ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ስደተኞች ከመብረራቸው በፊት የሕክምና እና የጥበቃ ምርመራዎችን የሚያካሂድ ሲሆን በተጨማም ለችግረኞች አስፈላጊ የሆኑ ሰብዓዊ ቁሳቁሶችን ያቀርባል።
አይኦኤም ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ስደተኞቹ የአዕምሮ ጤናን እና የስነልቦና ድጋፍን ጨምሮ የእርዳታ እና የጥበቃ አገልግሎት የሚሰጥበት የመቀበያ ማዕከል በአዲስ አበባ አቋቁሟል።
ስደተኞቹም ወደ መጡበት ማህበረሰቦቻቸው እንዲደርሱ ለመርዳት የገንዘብ እና የትራንስፖርት ድጋፍ ያገኛሉ።