ህወሓትን የሚቃወም እና መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሰልፍ ተካሄደ

ሰልፍ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

ዛሬ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ተሳታፊ የሆነበት ህወሓትን የሚቃወም እና የአገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሰልፍ ተካሄደ።

የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት በዚህ ሰልፍ ላይ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መስቀል አደባባይ ታድመዋል ብሏል።

በሰልፉ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች ህወሓትን የሚያወግዙ እና የአገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፉ መፈክሮችን ይዘው በመስቀል አደባባይ ታይተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅን አስመልክቶ ደስታቸውን በሰልፉ ላይ የገለጹ ሰዎች ታይተዋል።

በሰልፉ ላይ የታደሙ ሰዎች፤ 'ህወሓት የኢትዮጵያ ካንሰር ነው' 'የድላችን ምስጢሮች ፍትህ እና እውነት ናቸው' እንዲሁም 'ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት ጎን ነን' የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

ሰልፍ

በሰልፉ ላይ የከተማዋ ምክትል ከንቲባን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት የተገኙ ሲሆን፤ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰልፉ ላይ ባደረጉት ንግግር ሰልፉን ያስተባበሩትን የአዲስ አበባ ሴቶች እና ወጣቶች ማህበር አባላት እና አመራር እንዲሁም ድምፃቸውን ለማሰማት ማልደው የወጡትን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አመስግነዋል ብሏል የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት።

በሌላ በኩል መስቀል አደባባይ የተካሔደው ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል። የከተማዋ ፖሊስ በማሕበራዊ ገጹ ላይ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የከተማዋ ነዋሪ በትዕግስት እና በተባባሪነት መንፈስ የጸጥታ አካሉን በመደገፉ ምስጋና ይገባዋል ብሏል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

ለስምንት ወራት የተካሄደውን ጦርነት ለማብቃት የፌደራል መንግሥቱ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የመከላከያ ከትግራይ መውጣትን ተከትሎ የህወሓት ታጣቂዎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሱባቸውን ቦታዎች ለመያዝ በተለያዩ ስፍራዎች ጥቃት መክፈታቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

ይህም ግጭቱን ወደ አጎራባች ክልሎች እየወሰደው ይገኛል። የአፋር ክልል ከትግራይና ከአማራ ክልሎች ጋር በሚዋሰንበት አካባቢ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከሰባ ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል።