ኮቪድ-19፡ በአውስትራሊያ 'የስፖርት ልብሶቼ ኮቪድ-19ን ይከላከላሉ' ያለው ድርጅት 3.6 ሚሊየን ዶላር ተቀጣ

ታትሟል

አውስትራሊያዊው የስፖርት ልብስ ድርጅት ልብሶቹ 'ኮቪድ-19ን ይከላከላሉ፤ የወረርሽኙን ሥርጭትም ያስቆማሉ' በማለቱ 3.6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር [5 ሚሊየን የአውስትራሊያ ዶላር] ተቀጣ።

ይህ ማስታወቂያ የተሰራው በአውስትራሊያዊቷ የፋሽን ዲዛይነር ሎርና ጀን ነው።

ማስታወቂያው ልብሶቹ 'ኤልጂ' የተባለ አዲስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተሰሩ መሆኑን ጠቅሶ ይህም እንደ ቫይረስና ባክቴሪያ ያሉ ማንኛውንም ረቂቅ ተህዋስያንን ይከላከላል ይላል።

በዚህም ድርጅቱ 3.6 ሚሊየን ዶላር ቅጣት እንዲከፍል የአገሪቷ ፍርድ ቤት ውሳኔ አስተላልፎበታል።

በፍርድ ሂደቱ ወቅት ዳኛው የድርጅቱ ሃሳብ "በዝባዥ፣ ከሌሎች ገንዘብ ለመሰብሰብ ያለመ እና አደገኛ ነው" ብለውታል።

ማስታወቂያውን የሰራችው ሎርና ጄንም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቀብላለች።

ድርጅቱም ያሳሳተኝ ምርት የሚያቀርብልኝ ድርጅት ነው ብሏል።

የቢል ክላርክሰን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆነችው ሎርና "አንድ ታማኝ የምንለው ድርጅት ቃሉን አጥፎ ትክክለኛ ያልሆነ ምርት ሸጦልናል" ብላለች።

"አቅራቢው ኤልጂ የተሰኘውን አዲስ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተመረቱት ምርቶቹ በአውስትራሊያ፣ በአሜሪካ፣ በቻይና እና በታይዋን እየተሸጡ እንደሆነ እና ይህም ፀረ ባክቴሪያ እና ፀረ ቫይረስ መሆኑን እንድናምን አድርጎናል። እኛም ለደንበኞቻችን ጥቅም ስንል እናቀርባለን የሚል እምነት ነበረን" ብላለች ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ።

ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ያመራው ፋሽን ዲዛይነሯ ሎርና፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተስፋፋበት ባለፈው ሐምሌ ወር ልብሱን ማስተዋወቅ መጀመሯን ተከትሎ ነው።

ወደ ፍርድ ቤት ያመራውም በአውስትራሊያ ኮምፒቲሽን ኤንድ ኮንሱመር ኮሚሽን (ኤሲሲሲ) አማካኝነት ነበር።

አርብ ዕለት በታተመው የፍርድ ውሳኔ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛ፤ "ሎርና የተሳሰተ እና በሳይንስ ላይ ያልተመሰረተ ማስታወቂያ ላይ ደንበኞችን ወክላለች" ብለዋል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ድርጅቱ ለደንበኞቹ ሐሰተኛ እና አሳሳች ውክልና በማቅረቡ እና ሕብረተሰቡን በማሳሳቱ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

የኤሲሲሲ ሊቀ መንበር ሮድ ሲምስ በበኩላቸው "ይህ ምንም መሰረት በሌለው ነገር ላይ በሕብረተሰብ ጤና ላይ የተፈፀመ አስፈሪ ድርጊት ነበር" ብለዋል።

ድርጅቱም፤ የድርጅቱ መስራችና የፈጠራ ባለሙያዋ ሎርና ጀን ክላርክሶን፤ አዲሱን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ተመረተ የተባለውን የስፖርት ልብስ የማስታወቂያ ሥራዎችን ተቀብላ ማፅደቋን እንዲሁም በኢንስታግራም ገጿ በለቀቀችው ቪዲዮና በግል በሰጠቻቸው መግለጫዎቿ የተሳሳተ መልዕክቶች ማስተላለፏን አምኗል።

ዳኛውም ድርጊቱ በድርጅቱ ውስጥ ካለው ከፍተኛ አስተዳደር ደረጃ የመነጨ እና በመስራቿ ሎርና የተመራ መሆኑን ከግምት ውስጥ እንዳስገቡ ተናግረዋል።

የፋሽን ዲዛይነሯ ሎርና ትውልዷ በሰሜን ምዕራብ ኢንግላንድ ከተማ ላንካሻየር ሲሆን ሕጻን እያለች ነበር ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አውስትራሊያ የሄደችው። እዚያም የራሷን የንግድ ሥራ የጀመረችው ከ30 ዓመታት በፊት ነበር።

በመላው አውስትራሊያ፣ በኒውዚላንድ፣ በአሜሪካ እና በሲንጋፖር መደብሮች ያሏት ሎርና ጀን፤ የእርምት ማስታወቂያ እንድትሰራ ዳኛው ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ ለሦስት ዓመታት ያህል ከስፖርት ልብሱ ጋር በተዛመደ፤ አሳማኝ ምክንያት ከሌለ በስተቀር ማንኛውንም የፀረ ቫይረስ ማስታወቂያ እንዳይሰራ ታግዷል።

ባለፈው ሳምንት ድርጅቱ ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ ሕገ ወጥ የሆነ ማስታወቂያ ሰርቷል በሚል በሕክምና ቁሳቁሶች አስተዳደርና መድሃኒት ተቆጣጣሪ 29 ሺህ 454 የአሜሪካ ዶላር [40 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር] ተቀጥቷል።

ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ ይህ ዓይነቱ ማስታወቂያ በአውስትራሊያ ማሕበረሰብ ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ በመፍጠር ሰዎች ስለ ንፅህና እና ማሕበራዊ ርቀት መጠበቅ አሉታዊ ግንዛቤ እንዲያሳድሩ ያደርጋል ብሏል።