ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
4 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣ አልማዝ አጭበርብራ በጠጠር ለውጣለች የተባለች ሴት ተከሰሰች
ለንደን ከተማ ከሚገኝ የውድ ጌጣ ጌጥ መሸጫ መደብር ከ4.2 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ የሚገመት አልማዝ በጠጠር ለውጣለች የተባለች ሴት ፍርድ ቤት ቀረበች።
ሉሉ ላካቶስ የተባለችው የ60 ዓመት ሴት ቦድለስ ከተባለ መደብር ጠጠር በአልማዝ ለውጣ አጭበርብራለች የሚል ክስ ቀርቦባታል።
ግለሰቧ ሰባት አልማዞችን ከተመለከተች በኋላ አልማዞቹን በጠጠር ለውጣ ተሰውራለች የሚል ክስ በፍርድ ቤት ቀርቧል።
ግለሰቧ ይህን ድርጊት ፈጽማለች የተባለው ከ4 ዓመታት በፊት ነው።
"ክህሎት በተሞላበት መልኩ ጣቶቿን ተጠቅማ" አልማዞቹን ከቦርሳ ውስጥ አውጥታ ውዱን ጌጥ በጠጠር በመለወጥ በተመሳሳይ ቦርሳ በመክተት ስርቆት ፈጽማለች ሲሉ ዐቃቤ ሕግ ፍሊፕ ስኮት ተናግረዋል።
ትውልዷ በሮማኒያ የሆነችው እና ለረዥም ዓመት በፈረንሳይ የኖረችው ሉሉ ላካቶስ አልማዞቹን አልሰረቅኩም ስትል ተከራክራለች።
ለፍርድ ቤት በቀረበው የክስ አቤቱታ ላይ የጌጣ ጌጥ መሸጫ መደብሩ ኃላፊ በርካታ ገንዘብ ፈሰስ አድርጎ አልማዝ መግዛት ከሚፈልግ ሰው ጋር እንዲተዋወቅ ተደርጓል ይላል።
ከዚያም ኢንቨስት የሚያደርገው ግለሰብ የሚገዛቸውን አልማዞች ዋጋ የምትገምት ሴት ወደ መሸጫ መደብሩ እንድትመጣ ሆኗል ይላል ለፍርድ ቤቱ የቀረበው አቤቱታ።
ይህች የአልማዞቹን ዋጋ ትገምታለች ተብላ ወደ መደብሩ የመጣችው ሉሉ ላካቶስ ስትሆን፤ የመደብሩ ኃላፊ እና ሌሎች ሠራተኞች ባሉበት 7 አልማዞችን የያዘውን ቦርሳ በጠጠር በተሞላ ተመሳሳይ ቦርሳ ለውጣለች ተብሏል።
ዐቃቤ ሕግ ተከሳሿ አልማዙን ከወሰደች በኋላ እራሷን ለመቀየር መጠጥ ቤት ውስጥ የሚገኝ መጸዳጃ ቤት ገብታ፤ አድርጋ የነበረውን ኮፍያ እና ስካርፍ ጥላ፣ የለበሰችውን ልብስ ቀይራ ወደ ፈረንሳይ ተጉዛለች ብሏል።
መስከረም ወር ላይ በቁጥጥር ሥር የዋለችው ሴት ለእንግሊዝ ተላልፋ ተሰጥታ የክስ ሂደቷን እየተከታተለች ትገኛለች።