ኮቪድ-19፡ የቻይና ባለሥልጣናት ያልተከተቡ ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክ እንደማይችሉ አስታወቁ

ታትሟል

አንዳንድ የቻይና ባለሥልጣናት ሁሉም የቤተሰብ አባላቸው ሙሉ ክትባቱን ያልወሰዱ ተማሪዎች መስከረም ላይ ትምህርት ቤት መግባት እንደማይፈቀድላቸው ገለጹ።

በርካታ ከተሞችም ሰዎች እንደ ሆስፒታልና የገበያ ማዕከላት ያሉ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ለመግባት መከተብ አለባቸው ብለዋል።

በዚህም ቻይና በአንዳንድ ዘርፎች ላይ ክትባትን አስገዳጅ በማድረግ ፈረንሳይና ግሪክን ጨምሮ ሌሎች አገራትን ተቀላቅላለች።

ቻይና በዚህ ዓመት መጨረሻ 64 በመቶ የሚሆነውን ሕዝቧን ለመከተብ አልማለች።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ጉዋንዥ ግዛት "ያልተከተባችሁ ሰዎች ካላችሁ ልጆቻችሁን ከትምህርት ላለማስተጓጎል በአፋጣኝ መከተብ አለባችሁ" የሚል ማስታወቂያ አስነብባ ነበር።

እንደ ጂያንዢ እና ሔናን ያሉ ሎሎች ግዛቶችም ተመሳሳይ መመሪያ አውጥተዋል።

መስከረም ላይ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ የሚፈቀድላቸው ተማሪዎች ወላጆቻቸው የተከተቡ ናቸው ብለዋል።

ይሁን እንጅ ሕጉ ከክልል ክልል የተለያየ ነው።

የሰሜናዊ ሔቤ ግዛት በሆነችው ፒንጂያንግ እድሜያቸው ከ12 እስከ 17 ያሉ ተማሪዎች ሙሉ ክትባቱን ካልወሰዱ ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም። ይሁን እንጅ ይህ በሌላ የእድሜ ክልል የሚገኙ ተማሪዎችም ላይ ተግባራዊ ይሆናል አይሆንም የሚለው ግልጽ አይደለም።

በሻንዢ ግዛት ሃንቼንግ ደግሞ ያልተከተቡ ሰዎች ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች እና የመዝናኛ ሥፍራዎች እንዲገቡ አልፈቅድም ብላለች።

እነዚህ ሕጎች ተግባራዊ የሚሆኑበት የጊዜ ገደብ ግን ከከተማ ከተማ ይለያያል። ነገር ግን አብዛኞቹ በተያዘው የፈረንጆቹ ሐምሌ ወር መጨረሻ ድረስ ሰዎች ክትባታቸውን እንዲወስዱ ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል።

እነዚህ ውሳኔዎች የኦንላይን ማኅበረሰቡን አስቆጥተዋል። ውሳኔውን "ፍትሓዊ ያልሆነ" ሲሉም አጣጥለውታል።

አንድ ግለሰብ "መጀመሪያ ላይ ክትባቱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነው ብለው ነበር። አሁን ደግሞ አስገዳጅ ወደ መሆን ተቀየረ" ሲሉ በቻይናው ዊቡ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

የቻይና ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣናት በበኩላቸው ሰዎች ክትባቱን እንዲወስዱ ሊበረታቱ ቢገባም ውሳኔው ግን ለእነርሱ መተው አለበት ብለዋል።

ሆኖም ከታች ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚቻላቸው መጠን በርካታ ሰዎች ክትባቱን እንዲወስዱ ማድረግን ቅድሚያ እንዲሰጡ ተነግሯቸዋል።

ቻይና እስካሁን ከ1.4 ቢሊየን በላይ የኮቪድ-19 ክትባት የከተበች ሲሆን፤ የጤና ኮሚሽኑ ምን ያህል ሰዎች ሙሉ ክትባቱን እንደወሰዱ አልገለጸም።