ቻይና ጭቆናን አትቀበልም ሲሉ ፕሬዘዳንቷ ተናገሩ

ታትሟል

ቻይና ሌሎች አገሮችን አትጨቁንም ሲሉ ፕሬዝዳንቷ ሺ ጂንፒንግ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ 100 ኛ ዓመት የምስረታ መታሰቢያ በዓል ላይ ባሰሙት ንግግር ላይ ገለፁ ፡፡

ሺ በተጨማሪም ‹‹ጉልበተኞች›› በማለት ለአሜሪካ የተሰጠ በሚመስል ማስጠንቀቂያ ‹‹ጭንቅላታቸውን በታላቅ የብረት ግድግዳ ላይ ያነጥፋሉ›› ብለዋል፡፡

ይህ የፕሬዚዳንቱ አስተያየትም ከ 70 ሺህ ተመልካቾች ጭብጨባ ተለግሶታል፡፡

በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው ግንኙነት በተለይ በታይዋን ጉዳይ ላይ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የምትከተለው ታይዋን ራሷን እንደ ሉዓላዊ ሀገር ብታይም ቤጂንግ ደሴቲቱን እንደ አንድ አውራጃ ትመለከታለች ፡፡

ቤጂንግ ደሴቲቱን ለመመለስ ኃይል የምትጠቀም ከሆነ የአሜሪካ ሕግ ታይዋን ራሷን ለመከላከል ድጋፍ እንድታደርግ ያስገድዳል ፡፡ ፕሬዘዳንቱ ቻይና ከታይዋን ጋር ለመዋሃድ ‹‹የማይናወጥ ቁርጠኝነቷን›› ይዛ እንደቀጠለች ተናግረዋል ፡፡

‹‹የቻይና ሕዝብ ብሔራዊ ሉዓላዊነቱን እና የግዛት አንድነቱን ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት፣ ፍላጎት እና ችሎታ ማንም አቅልሎ መመልከት የለበትም›› ብለዋል ፡፡

ሐሙስ ጠዋት በተካሄደው ሥነ ሥርዓትም ወታደራዊ የአውሮፕላን ትርኢቶች ፣ የመድፍ ሰላምታዎች እና የአርበኞች ዘፈኖች ተሰምተዋል፡፡

በርካታ ሰልፈኞች በቤጂንግ ቲያንመንመን አደባባይ ላይ የታዩ ሲሆን ብዙዎቹ ጭምብል አላደረጉም ፡፡

ሀገሪቱ ላለፉት ሳምንታት በፓርቲው ፀድቆ የታተመውን የቻይና ታሪክ በመገናኛ ብዙሃን ሲተላለፍ ቆይቷል፡፡

ሆንግ ኮንግም በተመሳሳይ ቀን ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ለቻይና ተላልፋ የተሰጠችበትን በዓል እያከበረች ነው ፡፡

ፕሬዘዳንቱ ለአንድ ሰዓት ያህል በቆየው ንግግራቸውፓርቲው በዘመናዊ ቻይና ውስጥ ያለው ሚና ለአገሪቱ እድገት ማዕከላዊ እንደነበረና ፓርቲውን ከሕዝብ ለመነጠል የሚደረግ ሙከራም ‹‹እንደማይሳካ›› ተናግረዋል፡፡

ቻይናን ማዳን የሚችለው ሶሻሊዝም ብቻ ሲሆን ቻይናን ሊያለማ የሚችለው በቻይና መልክ የተቀረፀ ሶሻሊዝም ብቻ ነው ብለዋል ፡፡

አክለውም "ማንም ሰው ቻይናን እንዲገደብ ፣ እንዲጨቁን ወይም እንዲገዛ በጭራሽ አንፈቅድም" ብለዋል ፡፡

‹‹ይህንን ለማድረግ የሚደፍር ማንኛውም ሰው ከ 1.4 ቢሊዮን በላይ የቻይና ህዝብ በተሰራው ታላቁ የብረት ግንብ ጋር ጭንቅላቱን ያፋጥጣል ›› ብለዋል፡፡

ቻይና አሜሪካ እድገቷን ለመግታት እየሞከረች መሆኑን በተደጋጋሚ ትከሳለች - እነዚህ አስተያየቶችም ዋሽንግተንን እንደ ማጣቀሻ ተደርገው ይታያሉ ፡፡