በባንግላዲሽ ባጋጠመ የእሳት አደጋ ከ50 በላይ ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

በባንግላዲሽ አንድ ፋብሪካ ውስጥ በደረሰ የእሳት አደጋ ምክንያት 52 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ተጨማሪ 30 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ተቋማት አስታወቁ።

እሳት አደጋው የተነሳው 'ሀሺም ፉድ ኤንድ ቤቨሬጅ' በተባለው ፋብሪካ ላይ ሐሙስ ሌሊት ሲሆን፤ የአደጋው ምክንያት ደግሞ በፋብሪካው ውስጥ ተጠራቅመው የነበሩ ኬሚካሎችና ፕላስቲኮች መሆናቸውን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ከዋና ከተማዋ ዳካ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ፋብሪካ በደረሰው ጉዳት የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችልና እስካሁንም የት እንዳሉ የማይታወቁ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ኃላፊዎች ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ገልጸዋል።

የእሳት አደጋው ከመድረሱ በፊት ባለ ስድስት ፎቁ ፋብሪካ የፍራፍሬ ጭማቂ፣ እሽግ ፓስታና ማጣፈጫ በብዛት ያመርት ነበር ተብሏል።

ምንም እንኳን በርካታ የፋብሪካው ሠራተኞች የእሳት አደጋው ከመጀመሩ በፊት ቀን ላይ ሥራቸውን ጨርሰው የሄዱ ቢሆንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ግን የምሽት ተረኞች ሆነው እየሠሩ ነበር።

የዓይን እማኞች ለመገናኛ ብዙኃን ሲገልጹ ከእሳት አደጋው ለማምለጥ ከፎቅ ላይ በመስኮት በኩል ሲዘልሉ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

ወደ ፋብሪካው ጣሪያ የሚወስደውና ሰዎችን ሊያድን ይችል የነበረው በር በመቆለፉ ምክንያት በርካቶች ከአደጋው ማምለጥ እንዳቃታቸው የአካባቢው ባለሥልጣናት ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ገልጸዋል።

በባንግላዲሽ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእሳት አደጋ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ሲሆን እስካሁንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

በአውሮፓውያኑ 2013 በአንድ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ባጋጠመ የእሳት አደጋ ከ1100 በላይ ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ መንግሥትም በወቅቱ አፋጣኝ የማሻሻያ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ገልጾ ነበር።

ነገር ግን በአገሪቱ ያለው የሥራና መኖሪያ አካባቢዎች ደኅንነት አሁንም አሳሳቢ ነው።