የሊባኖስ ዋነኛ ኃይል ማመንጫዎች ሥራ በማቆማቸው መብራት ተቋረጠ

ታትሟል

በሊባኖስ ሁለት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ሥራ በማቆማቸው ሳቢያ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል መብራት ጠፍቷል።

ሁለቱ ማመንጫዎች ነዳጅ በመጨረሳቸው ነው አገልግሎት መስጠት ያቆሙት። በሊባኖስ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ስላለ ከአገር ውጭ ለሚገኙ የኃይል አቅራቢ ድርጅቶች ገንዘብ መክፈል አልተቻለም።

የመድኃኒት መደብሮች የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ስለገጠማቸው የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል።

ዴር አማር እና ዛህራኒ የተባሉት ኃይል ማመንጫዎች የሊባኖስን 40 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ይሸፍናሉ። እነዚህ ኃይል ማመንጫዎች መሥራት ያቆሙት አርብ ዕለት እንደሆነ ተገልጿል።

ሁለቱን የኃይል ማመንጫዎች የሚያስተዳድረው ኤሌክትሪሲት ዱ ሊባን (ኢዲኤል) የተባለ ድርጅት ነው። ኃይል ማመንጫዎቹን የሚያንቀሳቅስ ነዳጅ ጭነው የነበሩ መርከቦች በዶላር ካልተከፈላቸው ነዳጁን እንደማያወርዱ ተናግረዋል።

ዛህል በተባለት የሊባኖስ ከተማ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ፍጆታቸውን እንዲቀንሱ ተጠይቀዋል።

በአገሪቱ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቋረጥ በተጨማሪ ውሃም በፈረቃ መከፋፈል ጀምሯል።

ባለፉት 18 ወራት ሊባኖስ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ገጥሟታል። መገበያያቸው የሊባኖስ ፓውንድም ዋጋ አጥቷል።

የካንሰር እና የልብ ሕክምና የሚሰጡ አንዳንድ ሆስፒታሎች የመድኃኒት እጥረት ገጥሟቸዋል።

የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉት መድኃኒት መደብሮች ማኅበር እንደሚለው በመዲናዋ ቤይሩት 80 በመቶ የመድኃኒት መደብሮች ተዘግተዋል።

ከዕለት ወደ ዕለት በአገሪቱ የኑሮ ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመጣባት ሊባኖስ፤ ግማሽ ያህሉ ዜጎች በድህነት ውስጥ እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል። በአገሪቱ በሙስና የተወነጀሉ ፖለቲከኞች ከሥልጣን እንዲወርዱ በሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎችም ትናጣለች።

ላለፉት አስር ዓመታት በሊባኖስ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሲቆራረጥ ነበር። መብራት በፈረቃ ስለሚለቀቅ ነዋሪዎች ጄነሬተር ለመጠቀም ይገደዳሉ።

አሁን ግን አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በጨለማ ተውጧል።

ጄነሬተሮችን የሚያንቀሳቅስ ነዳጅ በቀላሉ ስለማይገኝ ጄነሬተርን እንደ አማራጭ መጠቀመም አይቻልም።