በናይጄሪያ በእገታ መበራከት ምክኒያት ትምህርት ቤቶች ተዘጉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሰሜናዊ ናይጄሪያ የምትገኘው የካዱና ግዛት ባለሥልጣናት ለእገታ ጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች በፍጥነት እንዲዘጉ አዘዙ።
ታጣቂዎች በክልሉ ከሚገኘው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ 150 የሚጠጉ ተማሪዎችን ከጠለፉ አንድ ቀን በኋላ ነው ይህ ትዕዛዝ የተሰጠው። እንዲሁም እናትና አንድ ጨቅላ ሕፃን ከሆስፒታል ውስጥ ታግተው ተወስደዋል።
የፀጥታ ኃይሎች የተጠለፉ ሰዎችን ለመታደግ እና ጠላፊዎቹን ለመያዝ ጥረት እያደረጉ ነው።
የካዱና ግዛት ትምህርት ኮሚሽነር ሼሁ ኡስማን ሙሐመድ ለቢቢሲ እንደገለጹት ከፀጥታ አካላት ጥበቃ የ30 ደቂቃ የመኪና ጉዞ በላይ የሚርቁ ሁሉም ትምህርት ቤቶች አዲስ የፀጥታ እቅድ ወጥቶ እስከሚተገበር ድረስ እንዲዘጉ ታዘዋል።
ቀደም ሲል በሰሜን ናይጄሪያ የሚገኙ በርካታ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ቆይተው የነበረ ቢሆንም መሰል እርምጃዎች ግን የእገታ ቀውስን አልፈቱም።
ይህ ሰሜናዊው የናይጄሪያ ክፍል ከዚህ ቀምም ቢሆን ዝቅተኛ የተማሪዎች ቁጥር ያለበት አካባቢ ነው። ጉደዩን በቅርት የሚከታተሉ ባለሞያዎች እንደሚሉት ከሆነ እየጨመረ የመጣው የፀጥታ ቀውስ ችግሩን እያባባሰው ይገኛል።
ከታህሳስ ወር ጀምሮ ከ1000 በላይ ተማሪዎች ገንዘብ በሚጠይቁ አካላት ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን ወደ አስር የሚጠጉ ደግሞ በወንጀል ቡድን አባላት በጥይት ተመትተው ተገድለዋል።
በናይጄሪያ ያሉ ባለስልጣኖችም በአፈናው ውስጥ የተሳተፉ የታጠቁ ቡድኖችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ብሎም ለማሸነፍ እየታገሉ ነው።












