በሳምንት የአራት ቀን ሥራ በአይስላንድ 'እጅግ ስኬታማ' ሆኗል

ታትሟል

በአይስላንድ በሳምንት የአራት የሥራ ቀናት ሙከራዎች "እጅግ ስኬታማ" እንደሆኑና ሠራተኞችም ወደ አጭር የሥራ ሰዓታት እንዲሸጋገሩ አድርጓቸዋል ሲሉ ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡

ለአጭር ሰዓታት የሚከፈለው ተመሳሳይ ክፍያ የተከፈለባቸው ሙከራዎች የተካሄዱት እአአ በ 2015 እና በ 2019 መካከል ነው፡፡

በአብዛኛዎቹ የሥራ ቦታዎች ምርታማነቱ ተመሳሳይ መሆኑን ወይም መሻሻሉን ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

ሌሎች በርካታ ተመሳሳይ ሙከራዎች ስፔን እና በዩኒሊቨር ኒውዚላንድን ጨምሮ በመላው ዓለም በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡

በአይስላንድ በሬይካቪክ ከተማ ምክር ቤት እና በመንግስት የሚካሄዱት ሙከራዎች ከ 2500 በላይ ሠራተኞችን ያካተቱ ሲሆን ይህም ከአይስላንድ ሠራተኛው ህዝብ ቁጥር አንድ በመቶውን ያህል ይሆናል፡፡

ብዙዎቹ ከ 40 ሰዓት ሳምንታዊ የሥራ ሰዓት ወደ 35 ወይም 36 ሰዓት ተቀይረዋል ሲሉ የዩናይትድ ኪንግደሙ አውቶኖሚ እና የአይስላንዱ አሶሴሽን ፎር ሰስቴይነብል ዴሞክራሲ ገልጿል።

ጥናቶቹ የሠራተኛ ማህበራት የሥራ ዘይቤዎችን እንደገና እንዲያዩ አድረጓቸዋል። ከአይስላንድ ሠራተኞች 86 በመቶዎቹ በተመሳሳይ ደመወዝ ወደ አጭር ሰዓታት ተሸጋግረዋል አልያም መብቱን ያገኛሉ ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

ሠራተኞቹ የጭንቀት ስሜታቸው ዝቅተኛ እንደሆነ እና ድካም ተጋላጭ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። ጤናቸው እና የሥራ እና የተቀረው ህይወት ዘይቤ ሚዛኑ መሻሻል አሳይቷል፡፡

የአውቶኖሚ የምርምር ዳይሬክተር የሆኑት ዊል ስትሮንግ "ይህ ጥናት በመንግስት ዘርፍ በዓለም ላይ ትልቁ አጭር የስራ ሳምንት ሙከራ ከተደረገ በኋላ በሁሉም መልኩ እጅግ አስደናቂ ስኬት መገኘቱን ያሳያል" ብለዋል፡፡

"የመንግሥት ዘርፉ አጭር የሥራ ሳምንቶች ፈር ቀዳጅ ለመሆን ዝግጁ መሆኑን ከማሳየት ባለፈ ለሌሎች መንግስታትም ትምህርት ማግኘት ያስቻላል፡፡"

የአሶሴሽን ፎር ሰስቴይነብል ዴሞክራሲ ተመራማሪው ጉድመንድር ዲ ሃራልድሰን "የአይስላንዳዊ አጭር የስራ ሳምንት ጉዞ በዘመናዊው ዓለም አነስተኛ ሰዓት መሥራት መቻል ብቻ ሳይሆን በሂደትም ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ይነግሩናል" ብለዋል፡፡

በኮሮናቫይረስ ተግዳሮቶች ሳቢያ ስፔን በከፊል ኩባንያዎች በሳምንት የአራት ቀን ሥራ በመሞከር ላይ ትገኛለች፡፡

በኒውዚላንድ የሚገኘው ዩኒሊቨርም ሠራተኞቹ በሙከራ ጊዜው ደመወዛቸውን ሳይነካ የሥራ ሰዓታቸውን በ 20 በመቶ እንዲቀንሱ ዕድል እየሰጠ ነው፡፡

በ4 ዴይ ዊክ ዘመቻ እአአ በግንቦት ይፋ በተደረገ ሪፖርት ለአጭር ሰዓታት መሥራት የእንግሊዝን የካርቦን ሊቀንሰው እንደሚችል ጠቁሟል፡፡