ከታሊባን ጋር በተደረገ ግጭት የአፍጋኒስታን ወታደሮች ወደ ጎረቤት አገር ሸሹ

ታትሟል

ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአፍጋኒስታን ወታደሮች ከታሊባን ታጣቂዎች ጋር መጋጨታቸውን ተከትሎ ወደ ጎረቤት አገር ታጂኪስታን መሸሻቸውን ባለስልጣናት አስታወቁ።

ወታደሮቹ ድንበር ተሻግረው ያፈገፈጉት ሕይወታቸውን ለማዳን እንደሆነ የታጂኪስታን ድንበር ጥበቃ መስሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ ያትታል።

በአፍጋኒስታን ግጭትና ሞት እየተበራከተ የመጣ ሲሆን ታሊባን ደግሞ በርካታ አካባቢዎችን በመቆጣጠር ላይ ይገኛል። በተለይ ደግሞ በቅርብ ሳምንታት ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍሎችን ታሊባን በፍጥነት እየተቆጣጠረ ነው።

ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ ከ20 ዓመታት በኋላ አሜሪካ፣ ዩኬ እና ወዳጆቻቸው አገሪቱን ለቅቀቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

የፊታችን መስከረም ጠቅልሎ ለመውጣት የተቀመጠው ቀነ ገደብ ከመድረሱ በፊት አብዛኛው የሚባለው የነዚህ አገራት ወታደሮች ከአፍጋኒስታን እየወጡ ይገኛል።

የወታደሮቹን መውጣት ተከትሎ የአፍጋኒስታን መከላከያ ሙሉ አገሪቱን ለመቆጣጠርና ደህንነት ለማስጠበቅ ሊቸገር ይችላል እየተባለ ነው።

አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና የኔቶ አባል አገራት ከታሊባን ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት ሙሉ ወታደሮቻቸውን ለማስወጣት የተስማሙ ሲሆን በምላሹ ደግሞ ታሊባን ማንኛውም አይነት አክራሪ ቡድን አገራቱ በሚቆጣጠሩት አካባቢ እንዳይኖር ለመከላከል ቃል ገብቷል።

ነገር ግን ታሊባን በዚህ ስምምነት ላይ ከአፍጋኒስታን ወታደሮች ጋር አልዋጋም አላለም ነበር። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ሰአት አንድ ሶስተኛ የሚሆነው የአገሪቱ ክፍል በታሊባን ቁጥጥር ውር ይገኛል።

ከ1000 ሺ በላይ የሚሆኑት የአፍጋኒስታን ወታደሮች ሸሽቶ ወደ ጎረቤት አገር መግባት በሶስት ቀናት ውስጥ ይህኛውን ሶስተኛው ያደርገዋል። በአጠቃላይ 1600 ወታደሮች ድንበር ተሻግረው ህይወታቸውን ለማዳን ሞክረዋል።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እስከ መስከረም ድረስ አፍጋኒስታንን ለቆ ለመውጣት ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት ለቆ የማይወጣና በአፍጋኒስታን የሚቀር ከሆነ ደግሞ ማንኛውም የውጪ አገር ሠራዊት እንደ ጠላት እንደሚታይ ታሊባን ማስጠንቀቁ የሚታወስ ነው።

ኔቶ በአፍጋኒስታን ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ወታደራዊ ተልዕኮ አጠናቋል። ነገር ግን ታሊባን ተጨማሪ ግዛቶችን እየተቆጣጠረ በመምጣቱ በአገሪቱ ውስጥ ሁከት እየጨመረ መጥቷል።

የታሊባን ቃል አቀባይ ሱሃይል ሻህን ካቡልን በጦር ኃይል መያዝ "የታሊባን ፖሊሲ አይደለም" ካሉ በኋላ፤ ኳታር ውስጥ ከሚገኘው የታጣቂ ቡድኑ ጽህፈት ቤት ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት፤ የመውጫ ቀነ ገደቡ ከተጠናቀቀ በኋላ ወታደራዊ ተቋራጮችን ጨምሮ የትኛውም የውጭ ኃይል መቆየት የለባቸውም ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ ወታደሮች ሙሉ በሙሉ መስከረም 9 ቀን እንዲወጡ ቀነ ገደብ ያስቀመጡ ሲሆን፤ ይህም የ9/11ዱ ጥቃት 20ኛ ዓመቱ የሚከበርበት እለት ነው፡፡

የአሜሪካ ጦር ለምን በአፍጋኒስታን ተገኘ?

እአአ መስከረም 11/2001 በአሜሪካ በተፈጸመ ጥቃት ወደ 3,000 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። የአልቃይዳ መሪ የነበረው ኦሳማ ቢን ላደን ከጥቃቱ ጀርባ መሆኑ ታወቀ።

አክራሪዎቹ ታሊባኖች አፍጋኒስታንን ሲያተዳድሩ የነበረ ሲሆን ቢንላደንን አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ከመስከረሙ 9/11 ጥቃት ከአንድ ወር በኋላ አሜሪካ በአፍጋኒስታን የአየር ድብደባ ጀመረች።

ሌሎች ሀገራትም ጦርነቱን የተቀላቀሉ ሲሆን ታሊባንም በፍጥነት ከስልጣን ተወግዷል። ከስልጣን ቢወርዱም ጠፍተው አልጠፉም እንዲያውም ተጽዕኗቸው እያደገ ነው።

በኋላም አሜሪካ እና አጋሮቿ የአፍጋኒስታንን መንግሥት ከመፍረስ ለማስቆም እና በታሊባን የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ሲጥሩ ቆይተዋል።