ቦይንግ 737 የጭነት አውሮፕላን ባህር ላይ ወደቀ

ታትሟል

ሁለት ሰዎችን ያሳፈረ ቦይንግ 737 የጭነት አውሮፕላን ባጋጠመው የሞተር ችግር በሃዋይ የባህር ዳርቻ ወደቀ።

አውሮፕላኑ ከሆንሉሉ ተነስቶ ወደ ማዊ ደሴት ሲጓዝ ነበር። ከዳንኤል ኬ ኢኑዬ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደተነሳ ወዲያውኑ ውሃው ላይ ወድቋል።

የባህር ጥበቃ አባላት ሁለቱን አብራሪዎች አርብ ዕለት ከባህር ላይ ታድገዋቸዋል።

አንደኛው አበራሪ በአውሮፕላኑ ጭራ ላይ ተጣብቆ ከነበረበት በአውሮፕላን እገዛ ወደ ሆስፒታል መወሰዱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ይህ አብራሪ ለሕይወቱ አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በመገኘቱ ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል ተወስዷል ተብሏል።

ሌላኛውን ፓይለት በጀልባ በመታገዝ ማትረፍ እንደተቻለ ኤችኤንኤን ገልጿል። ይህም አብራሪ ጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምከንያት በአስጊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።

ኤንቢሲ ባሰራጨው ምስል ከአውሮፕላን አብራሪዎች አንዱ ነው ተብሎ የሚገመት ሰው በተሽከርካሪ ወንበር ሲወሰድ ታይቷል። ግለሰቡ ህሊናውን ያልሳተ ይመስላል ተብሏል።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ቦይንግ ስለጉዳዩ በቅርበት ከባለስልጣናት ጋር እየተገናኘን "ሁኔታውን እየተከታተለ" ነው ብሏል በመግለጫው።

የፌደራል አቪየሽን ኤጀንሲ ከብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ ጋር አደጋውን ይመረምራሉ ተብሏል።

የበረራ መከታተያ ድረ-ገጹ ፍላይትራዳር24 እንዳለው 737-200 የጭነት አውሮፕላን እአአ ከ 2014 ጀምሮ እቃ ሲያጓጉዝ ቆይቷል።

የትራንሳይየር በረራ ቁጥር 810 ከሆንሉሉ ወደ ካህሉይ መብረር ቢጀምርም በፍጥነት ለመመለስ ቢሞክርም አውሮፕላኑ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎችን በኋላ ውሃ ላይ ወድቋል።

ትራንሳይየር ከ 1982 ጀምሮ በሥራ ላይ የተሰማራ ሲሆን ከሀዋይ ትልቁ የአየር ጭነት አገልግሎት ሰጪዎች አንዱ ነው። አምስት ቦይንግ 737 አውሮፕላኖችም አሉት ተብሏል።

ይህ አውሮፕላን ሁለት ጊዜ በደረሰበት የመከስከስ አደጋ ምክንያት እንዳይበር ከታገደው ከቦይንግ 737 ማክስ ጋር ተመሳሳይ አይደለም።

737 ማክስ እኤአ በ 2020 በአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች እንደገና እንዲበር ቢፈቀድለትም በድጋሚ ፈተናዎች ገጥመውታል።