ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ ክትባት፡ የአውሮፓ ሕብረት ክትባት አምራቹን አስትራዜኔካን ለምን ወደ ፍርድ ቤት ወሰደው?
የአውሮፓ ሕብረት በሰኔ ወር መጨረሻ 120 ሚሊዮን ብልቃጥ አስትራዜኔካ ክትባት ለአባል አገራቱ እንዲደርስ ለማስገደድ ያደረገው የሕግ ክርክር ሳይሳካ ቀርቷል።
ቤልጂየም የሚገኘው ፍርድ ቤት አስትራዜኔካ እስከ መስከረም ድረስ 80 ሚሊዮን ብልቃጥ ማድረስ አለበት የሚል ውሳኔ አሳልፏል። ይህ ግን የአውሮፓ ሕብረት ከጠየቀው በእጅጉ ያነሰ ነው።
ፍርድ ቤቱ ምን ወሰነ?
ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ አስትራዜኔካ በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ካስረከበው 30 ሚሊዮን በተጨማሪ መስከረም መጨረሻ ድረስ 50 ሚሊዮን የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን ለአውሮፓ ሕብረት ማድረስ አለበት።
በውሳኔው መሠረት ኩባንያው ማቅረብ ያለበት፡
- 15 ሚሊዮን ብልቃጥ እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ
- 20 ሚሊዮን ብልቃጥ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ
- 15 ሚሊዮን ብልቃጥ አስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ
እነዚህን ግዴታዎች የማያሟላ ከሆነ አስትራዜኔካ ባላቀረበው የክትባት የብልቃጥ መጠን 10 ዩሮ ቅጣት ይከፍላል።
ስለውሳኔው ምን ተባለ?
አስትራዜኔካ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በደስታ ተቀብሎ ሰኔ ወር መጨረሻ ደረስ ከ80 ሚሊዮን በላይ ክትባቶችን እንደሚያቀርብ ገልጿል።
"በአውሮፓ ኮሚሽን የተጠየቁት ሌሎች እርምጃዎች በሙሉ ውድቅ የተደረጉ ሲሆን በተለይም ፍርድ ቤቱ የአውሮፓ ኮሚሽን ከሌሎቹ ስምምነት ፈራሚ አካላት የተለየ ወይም የቅድሚያ መብት የለውም" ብሏል።
የአውሮፓ ኮሚሽን ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በላይ እንዲደርሰው ይፈልግ ነበር። በጠቅላላው አስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 120 ሚሊዮን እንዲሁም እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ 300 ሚሊዮን ብልቃጦች እንዲደርሱት ይፈልጋል።
ኮሚሽኑ ውሳኔውን እንደ ድል ቆጥሮታል። የህብረቱ ኮሚሽነር ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን በሰጡት አስተያየት "ውሳኔው የኮሚሽኑን አቋም ያረጋግጣል። አስትራዜኔካ በውሉ የገባውን ቃል አላከበረም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የአውሮፓ ሕብረት-አስትራዜኔካ ክርክር እንዴት ተጀመረ?
የአውሮፓ ሕብረት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በተፈረመው የ300 ሚሊዮን ብልቃጥ ክትባት ውል ምክንያት ከአስትራራዜኔካ ጋር ስምምነት ጠፍቶ ነበር። በ2021 መጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት መድረስ ከነበረበት 90 ሚሊዮን ብልቃጥ የአውሮፓ ኮሚሽን እጄ የገባው 30 ሚሊዮን ብቻ ነው ይላል።
በዓመቱ ሁለተኛ ሩብ ዓመት ደግሞ አስትራዜኔካ ቃል ከገባው 180 ሚሊዮን ዶዝ 70 ሚሊዮን ብቻ ማድረስ እችላለሁ ይላል።
ሚያዝያ ላይ የአውሮፓ ኮሚሽን የክትባቱን አቅርቦት ውል ባለማክበሩ እና አቅርቦቶችን በወቅቱ ለማድረስ "አስተማማኝ" ዕቅድ ባለመኖሩ ኩባንያውን ከሷል። ሁሉም 27ቱ የአውሮፓ ሕብረት አገራት ሕጋዊ መንገዱን ደግፈዋል።
ዩናይትድ ኪንግደምስ?
የኦክስፎርድ-አስትራዛኔካ ክትባት በኦክስፎርድ እና በኬል እየተመረተ ነው። በዊሬክሃም የሚገኘው ሦስተኛው ማምረቻ ክትባቱን ወደ ብልቃጦች በማስገባት ለስርጭት ያዘጋጃቸዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም 100 ሚሊዮን ብልቃጥ አዛለች። ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ እዚያው ሲመረቱ 10 ሚሊዮን ብልቃጦች ከሕንዱ የሴረም ኢንስቲትዩት የሚቀርቡ ናቸው።
ዩናይትድ ኪንግደም ከዚህ ውስጥ ግማሹን የተቀበለች ሲሆን ግማሹ ሕንድ ካለችበት የኮቪድ-19 ችግሮች አንጻር መቼ እንደሚቀርቡ ግልጽ አይደለም።
ሌሎች ክትባቶችስ?
የፋይዘር ክትባት በአብዛኛው በቤልጂየም በሚገኘው በፑርስ የሚመረት ሲሆን በጀርመን ማርበርበርግም አንድ ማምረቻ ተገንብቷል። ዩናይትድ ኪንግደም 100 ሚሊዮን ብልቃጥ የፋዘርን ክትባቶችን አዛለች።
የአውሮፓ ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር የአውሮፓ ሕብረት 25 ሚሊዮን ብልቃጥ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መላኩን ቢገልጽም ወደ ሕበረቱ ስለተላኩት ግን አልተገለጸም። የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚላክ እገዳን ቢቃወሙም ከዚህ በተቃራኒው ወስነዋል።
ክትባቶች በአንድ ቦታ ሊመረቱ ቢችሉም "ተሞልተውና ተጠናቀው" ወደ ብልቃጦች ውስጥ ገብተው ወደ ውጭ ለመላክ የሚዘጋጁት በሌላኛው አገር ሊሆን ይችላል።
የሞደርና ክትባት በስዊዘርላንድ ተመርቶ በስፔን የሚታሸግ ነው። እንግሊዝ 17 ሚሊዮን የሞደርና ክትባቶችን አዛለች።
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን/ጃንሰን ክትባት የሚሠራው ኔዘርላንድስ ውስጥ ነው። ከዚህ ደግሞ ዩናይትድ ኪንግደም 30 ሚሊዮን ክትባቶችን አዛለች።
የሚያስፈልጉ አንዳንድ ግብዓቶች በሌላ ቦታ ሊመረቱ ይችላሉ።
ለምሳሌ የዩናይትድ ኪንግደም ኩባንያ ክሮዳ ፋይዘር ክትባቱን እንዲሠራ ግብዓት እያቀረበ ነው።