ባለጸጋዋ ማኬንዚ ስኮት ከሁለት ቢሊዮን በላይ ለበጎ አድራጎት አበረከተች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአማዞን መስራች ጄፍ ቤዞስ የቀድሞ ባለቤት የነበረችው ቢሊየነሯ ማኬንዚ ስኮት 2.7 ቢሊየን ዶላር ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለገሰች።
ማኬንዚ ስኮት የሰጠችውን ከፍተኛ መጠን ያለው የልገሳ ገንዘብን በተመለከተ በጻፈችው ጽሁፍ ላይ እንዳለችው ገንዘቡን "ከዚህ ቀደም ችላ ለተባሉና ከሚገባቸው በታች የገንዘብ ድጋፍ ላገኙ" የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የተበረከተ።
በዚህም መሠረት ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋውን ገንዘብ በዘር መካከል ባለው ያለመመጣጠን ዙሪያ፣ በጥበባትና በትምህርት ዙሪያ ለሚሰሩ 286 ድርጅቶች የተበረከተ ነው።
ማኬንዚ ስኮት በዓለማችን ላይ እጅጉን ሀብታም ከሆኑ ሴቶች መካከል የምትጠቀስ ናት።
አብዛኛው ሀብቷ የመጣው በአሁኑ ጊዜ የዓለማችን ቀዳሚ ባለጸጋ ከሆነው ጄፍ ቤዞስ ጋር የነበራት ጋብቻ ከሁለት ዓመት በፊት በፍቺ ሲቋጭ ከጋራ ሀብታቸው የተካፈለችው ገንዘብ ነው።
ማኬንዚ ስኮት የቀድሞ ባለቤቷ ጄፍ ከ25 ዓመታት በፊት የሀብቱ ምንጭ የሆነውን የቴክኖሎጂ ኩባንያውን አማዞንን ሲያቋቁም የረዳችው ሲሆንም በተፋቱበት ወቅት ግን በደረሱት ስምምነት ሚስት የኩባንያውን አራት በመቶ የባለቤትንት ድርሻ ብቻ ነው የያዘችው።
ማኬንዚ ስኮት ከዚህ በፊትም ከፍተኛ መጠን ያለውን ሀብቷን ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አበርክታለች።
በአራት ወራት ውስጥ ብቻም ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሴቶች ለሚመሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ለችግረኞች ምግብ ለሚያቀርቡና ለጥቁሮች ኮሌጆች ሰጥታለች።
ምንም እንኳን ከፍተኛ መጠን ያለውን ሀብቷን ለበጎ አድራጎት ተቋማት ብትለግስም ማኬንዚ ስኮት ወደ 60 ቢሊዮን ዶላር በሚጠጋ ገንዘቧ የዓለማችን 22ኛዋ የዓለማችን ባለጸጋ ለመሆን ችላለች።
በቅርቡ በጻፈችው ጽሁፏ ላይ አሁንም ያላትን ሀብት ለማከፋፈል ከፍ ያለ ፍላጎት እንዳለት ገልጻለች።
አስካሁን ከማኬንዚ ስኮት ልግስና በአንጻራዊ ሁኔታ ከፍተኛውን ገንዘብ ያገኙት በተለያዩ ሐይማኖቶች መካከል የለውን አለመግባባት ለማጥበብ የሚሰሩ ድርጅቶችና አንዳንድ ኮሌጆች እንዲሁም ዩኒቨርስቲዎች ናቸው።
ስኮት ካላት ሀብት አብዛኛውን በልግስና ለመስጠት ከሁለት ዓመት በፊት የዓለማችን ባለጸጋዎች ያላቸውን ሀብት መልሰው ለተቸገሩ ለመስጠት በሚገቡት ቃል መሰረት እሷም ቃል ገብታ ነበር።















