ባለ ብዙ መልኩ መስቀል አደባባይ በአዲስ ገጽታ

የፎቶው ባለመብት, AA City Press Secretary/FB
መስቀል አደባባይ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተከሰቱ ወሻኝ ዋና ዋና ታሪካዊ ክንውኖችን ያስተናገደ የአገሪቱ ዋነኛ አደባባይ ነው።
አደባባዩ በሐይማኖታዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በስፖርታዊ፣ በባህላዊ፣ በጥበባዊና በሌሎችም መስኮች ግዙፍ የሚባሉ ሁነቶችን ሲያስተናግድ በርካታ አስርታትን አሳልፏል።
ማርክሲስቱ ወታደራዊው መንግሥት ወደ ስልጣን መጥቶ በአመራርነት በቆየባቸው ዓመታት ስሙ ወደ አብዮት አደባባይነት ተቀይሮ ለ17 ዓመታት መቆየቱ አይዘነጋም።
በዚህ ወቅትም አደባባዩ ስሙን ያገኘበት የመስቀል በዓልም በአደባባዩ መከበሩ ቀርቶ ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋውሮ ቆይቶ ነበር።
መስቀል አደባባይ በየዓመቱ የሚከበረውን በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚታደሙበትንና በርካታ ቱሪስቶችን የሚስበው የደመራ ሥነ ሥርዓት የሚስተናገድበት ዋነኛ ሥፍራ ነው።
በንጉሡ ዘመንም ታላለቅ ሕዝባዊ ሥነሥርዓቶች የሚካሄድበትና የዘውዱ የክብር ዘብ ሠራዊት በበዓላትና በሌሎች ዝግጅቶች ላይ የሰልፍ ትርኢት የሚያሳይበት ነበር።
ከዚህ ባሻገር አደባባዩ በርካታ በታሪክ የሚዘከሩ ክስተቶችን አስተናግዷል።
ስሙ ተቀይሮ በነበረበት የደርግ ዘመን መስከረም ሁለት ቀን የአብዮት በዓል በደማቅ ወታደራዊ ትርኢቶች ታጅቦ የሌሎች ሶሻሊስት አገራት መሪዎች በሚገኙበት እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በስፍራው ሲከበር ቆይቷል።
በሰባዎቹ መጀመሪያ ላይ የሶማሊያ ጦር ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ዘልቆ በገባበት ጊዜ አገሩን ለመከላከል ከየአቅጣጫው የተሰባሰበው 'ሕዝባዊ ሠራዊት' ሥልጠነውን አጠናቆ ወደ ጦር ግንባር የሚያደርገው ሽኝት በታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ የተከናወነው በዚሁ አደባባይ ነበር።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረተ ድንጋይን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጉባ ላይ ካስቀመጡ በኋላ ለድጋፍ ለወጣው ሕዝብ ስለግድቡ ቀዳሚውን ንግግር ያደረጉት በመስቀል አደባባይ ነበር።
የአዲስ አበባ መስተዳደር በ2.5 ቢሊየን ብር በላይ በማውጣት በመስቀል አደባባይ ገጽታ ላይ ጉልህ የሚባል ለውጥ ያካሄደበትን የግንባታ ፕሮጀክት እሁድ ሰኔ 06/2013 አስመርቋል።
በርካቶች በመስቀል አደባባይና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ከተማን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ቀይሯል ብለው የመሰከሩለት ሥራ ታሪካዊውን አደባባይ አዲስ ገጽታን አላብሶታል።
የግንባታው መጠናቀቅን ተከትሎ በምረቃው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "መስቀል አደባባይ ዜጎች ከሁሉም የአገሪቱ ጫፍ የሚገናኙበት፣ ብዙ ታሪክ ያሳለፈ የሁላችንም አደባባይ ነው" ብለውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም "መስቀል አደባባይ ብዙ ያየ ብዙ ያሳለፈ የማንነታችን ክፋይ የመሰብሰቢያችን ሲሳይ ነው" በማለት አደባባዩ ብዙ ነገሮችን ያስተናገደ ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, AA City Press Secretary/FB
መስቀል አደባባይ
ስያሜውን ያገኘው በየዓመት በወርሃ መስከረም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበረው የመስቀል በዓል ነው።
በየዓመቱ መስከረም 16 የሚከበረውን የደመራ በዓል ለመታደም በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች እና ቱሪስቶች ወደ ቦታው ይተማሉ።
በዕለቱ ከሚከናወነው የደመራ ማብራት ሥነ ሥርዓት ጎን ለጎን ሐይማኖታዊ መዝሙሮች እና ትርዒቶችም ይቀርቡበታል።
የስያሜ ለውጥ
መስቀል አደባባይ የሚለው ስያሜ በደረግ ዘመን ተቀይሮ አብዮት አደባባይ ተብሎ ነበር።
የስም ብቻ ሳይሆን በቦታው ዓመታዊው የአብዮት በዓል እና የላብ አደሮች ቀን ሲከበርበት ቆይቷል።
በወቅቱ በአደባባዩ የተሰቀሉት የካርል ማርክስ፣ ፍሬድሪክ ኤግልስ እና የቭላድሚር ሌኒን ምስሎችም የሶሻሊስት ኢትዮጵያን የሚያመላክቱ እና ከብዙዎች አዕምሮ የማይጠፉ ናቸው።
ከደርግ ውድቀት በኋላ አደባባዩ ወደ ቀድሞ ስያሜው በመመለስ መስቀል አደባባይ የሚለውን ስም መልሶ ያዘ።

የፎቶው ባለመብት, Surafel Atnafu
ፖለቲካዊ ሥነ ሥርዓቶች ማካሄጃ
የተለያዩ ፖለቲካዊ ሥነ ሥርዓቶችና ክብረ በዓሎች በመስቀል አደባባይ ተካሂደዋል።
የቅርቡን ለማስታወስ እንኳን በምርጫ 97 ወቅት በኢህአዴግ እና በወቅቱ የተቃዋሚዎች ጥምረት የነበረውን የቅንጅትን እጅግ ከፍተኛ የተባለውን ሰልፍ አስተናግዷል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ሰኔ 16 የተጠራውን የድጋፍ ሰልም በዚሁ አደባባይ የተካሄደ ነው።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች የሚጠሯቸውን ሠልፎች በመደገፍ ብዙዎች ወደ መስቀል አደባባይ በማቅናት ተቀላቅለዋል።
መስቀል አደባባይ ምንም እንኳን በአብዛኛው መንግሥትን የሚደግፉ ሰልፎችን ቢያስተናግድም ጥቂት የማይባሉ ጸረ መንግሥት ተቃውሞዎች ተሰምተውበታል።
የሽኝት ቦታ
መስቀል አደባባይ የአገሪቱ ታላላቅ ሰዎች ሲያርፉ ታላቅ የክብር ሽኝት ለማድረግም አገልግሏል።
ታላቁ ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ ህይወቱ ባለፈበት ወቅት በሺህዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎቹ በመስቀል አደባባይ ተገኝተው የክብር ሽኝት አድርገውለታል።
ቀድመው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈትን ተከትሎም ሺህዎች ወደዚሁ አደባባይ በመውጣት ሽኝት አድርገዋል።
ታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥር አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መኪናቸው ውስጥ እያሉ ህይወታቸው አልፎ የተገኘውና ሽኝታቸውም የተከናወነው በዚሁ ታሪካዊ አደባባይ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሙዚቃ ድግስ
የአገሪቱ ታላላቅ አርቲስቶች የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ለመቅረቢያነት ከሚመርጧቸው ቦታዎች አንደኛው መስቀል አደባባይ ነው።
በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሙዚቃ ድግስ በቦታው ተደርጓል።
በቅርቡ እንኳን ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የሙዚቃ ዝግጅቱን በሺህዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎቹ በተገኙበት በዚሁ በመስቀል አደባባይ አቅርቧል።
የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሊ 75ኛ ዓመት የልደት በዓልም ቤተሰቦቹ እና ሌሎች ታዋቂ ሙዚቀኞች በተገኙበት በዚሁ ስፍራ ተካሂዷል።
የስፖርት ስፍራ
መስቀል አደባባይ ለጤናቸው ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ከሚያደርጉ ግለሰቦች ጀምሮ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች የሚካሄዱበት ስፍራ ነው።
በተለያዩ ምክንያቶች አልፎ አልፎ ቦታው ከመቀየሩ ውጪ ታላቁ ሩጫ ውድድር ማስጀመሪያ እና መጨረሻም ይኸው አደባባይ ነው።
የመኪና እና የብስክሌት ውድድርም ቦታው ላይ ሲካሄድ መመልከት አዲስ አይደለም።
ታዳጊዎች በቡድን በቡድን እግር ኳስ ሲጫወቱ አገራቸውን በሩጫ ለማስጠራት የሚጥሩ አትሌቶችም ልምምዳቸውን የሚያደርጉበት ስፍራ ነው።

የፎቶው ባለመብት, William Campbell
ሙዚየም
በመስቀል አደባባይ ሁለት ሙዚየሞችን ይገኛሉ።
የመጀመሪያው አዲስ አበባ ሙዚየም ነው። ሙዚየሙ እአአ በ1986 የተመሠረተ ሲሆን የከተማዋን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች መዝግቦ ለማቆየት የተቋቋመ ነው።
ሁለተኛው ሙዚየም የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም ነው። ሙዚየሙ ከአስራ አንድ ዓመት በፊት የተቋቋመ ነው። በደርግ ሥርዓት ወቅት ህይወታቸውን ላጡ የቀይ ሽብር ሰማዕታት ማስታወሻነት የተቋቋመ ሲሆን የሬሳ ሳጥን፣ የተገደሉ ሰዎች ፎቶዎች እና ሌሎችንም ቁሳቁሶች ሰብስቦ ይዟል።
እንደ ማጠቃለያ
መስቀል አደባባይ ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ የተለያዩ አገልግሎት እና ታሪካዊ ሁኔታዎች የተፈጸሙበት ቦታ ነው።
የተለያዩ ማስታወቂያዎች በትልልቅ ቢልቦርዶች ከሚሰቀሉባቸው የአዲስ አበባ ቦታዎች መስቀል አደባባይ አንዱ ነው።
ቀደም ሲል የታክሲ መጫኛ እና ማውረጃ በመሆን ያገለገለ ሲሆን አሁን ደግሞ ረዥም ርቀት ተጓዥ አውቶብስ መንገደኞችን መጫኛ እና ማውረጃ ሆኖ ያገለግላል።
መስቀል አደባባይ ለአንዳንዶች መቀጣጠሪያ ለሌሎች ደግሞ ጊዜ ማሳለፊያ ቦታ በመሆንም ያገለግላል።















