ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አውስትራሊያ ስደተኛ የቤተሰብ አባላትን እንድትለቅ ጫና ተደረገባት
አውስትራሊያ ደሴት ላይ አስራ የያዘቻቸው የቤተሰብ አባላትን እንድትለቅ ጫና ተደረገባት።
የቤተሰብ አባላቱ ክሪስማስ ተብሎ በሚጠራ ደሴት ላይ የሚገኙ ሲሆን ከቤተሰብ አባላቱ መካከል አንዲት የሦስት ዓመት ልጅ በጽኑ መታመሟን ተከትሎ ነው በአውስትራሊያ መንግሥት ላይ ጫናው የበረታው።
ታርኒካ ሙሩግፓና የተባለችው የሦስት ዓመት ልጅ በሳንባ ምች በሽታ ከተጠቃች በኋላ ከደሴቷ ለተጨማሪ ሕክምና ወደ አውስትራሊያ ፐርዝ ከተማ ተወስዳለች።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ታዳጊዋ ፈጣን እና ተገቢ ሕክምና ሳታገኝ ቆይታለች በማለት በአውስትራሊያ መንግሥት ላይ የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።
የሦስት ዓመቷ ሕጻን ለ10 ቀናት ታማ ከቆየች በኋላ በደሴቱ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ከተወሰደች በኋላ ነበር ወደ ፐርዝ ለተጨማሪ ሕክምና የተላከችው።
የታዳጊዋ እናት ፕሪያ ናዴሳሊንግደራም ሐኪሞች ልጇን በሆስፒታል እንዲያክሙላት በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ዶክተሮች ፓራሴታሞል እና አይብፕሮፌን እንክብሎችን ብቻ እንደሰጧት ተናግራለች።
የአውስትራሊያ ባለሥልጣኖች በበኩላቸው ታርኒካ በደሴቱ የሚያስፈልጋትን ሕክምና አግኝታለች ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የጥገኝነት ጥያቄ
የሦስት ዓመቷ ልጅ የሕክምና ጉዳይ ስለ ቤተሰቡ የጥገኝነት ጥያቄ ሕዝቡ በድጋሚ ጥያቄ እንዲያነሳ ምክንያት ሆኗል።
ቤተሰቦቿ ከሲሪ ላንክ በጀልባ አውስትራሊያ ገብተው ጥገኝነት ከጠየቁ ከአሥር ዓመታት በላይ አልፏቸዋል።
አውስትራሊያ ከገቡ በኋላ በኩዊንስላድ ግዛት፣ ቢሎላ ከተማ እየኖሩ ሳለ ነው ሁለቱ ልጆቻቸው ታርንካ እና ኮፒካን የወለዱት።
ቤተሰቡ ወደ ክሪስመስ ደሴት የተዛወረው ፍርድ ቤት ከአገሪቱ እንዳይወጡ መወሰኑን ተከትሎ እአአ በ2019 ነበር።
ይኖሩበት የነበረው ቢሎላ ከተማ አስተዳደር ከከተማው እንዳይወጡ ትግል አድርጓል። ጉዳያቸውም በአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እንዲታይ አድርጓል።
የታርኒካ እናት ፕሪያ ከልጇ ጋር ፐርዝ ሆስፒታል እንድትሄድ ቢፈቀድላትም አባቷ ናድስ እና እህቷ ኮፒካ ደሴቱ ውስጥ እንዲቀሩ ተወስኗል።
የልጅቷ መታመም ተቃዋሚ ሕግ አርቃቂዎችን ጨምሮ ብዙዎች መንግሥት ስደተኞቹን እንዲለቅ እንዲጠይቁ አነሳስቷቸዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ካረን አንድሪውስ ቤተሰቡ አውስትራሊያ እንዲኖር ቪዛ የመስጠት ሥልጣን አላቸው።
"ቤተሰቡ መታገት የለበትም። በቢሎላ ከተማ መኖር ይገባቸዋል" ሲሉ ቃል አቀባይ ክሪስቲና ካንሊ ተናግረዋል።
ቤተሰቡ አሜሪካ ወይም ኒው ዚላንድ ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ ሐሳብ እንዳለው የአውስትራሊያ መንግሥት ተናግሯል። ሆኖም ግን የቤተሰቡ ጠበቃ ካሪና ፎርድ እሷም ይሁን ቤተሰቡ ይህ አማራጭ እንዳልቀረበላቸው ገልጸዋል።
የቤተሰቡ ደጋፊዎች ክዊንስላንድ ወዳለው ቤታቸው እንዲመለሱ ነው ፍላጎታቸው።
የአውስትራሊያ ፖሊሲ
አውስትራሊያ በጀልባ ወደ ግዛቷ የሚገቡ ስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ አትቀበልም።
የአገሪቱ መንግሥት ይህንን የስደተኞች ፖሊሲ ያወጣሁት ሕገ ወጥ የሰው ዝውውርን ለመግታት ነው ይላል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን የስደተኞችን መብት የጣሰ ፖሊሲ ነው ብለው ይተቹታል።
የአውስትራሊያ ፖሊሲ "ዜጋ ያልሆኑ ሕገ ወጦች" የሚላቸውን ግለሰቦች የማሰር መብትን ለመንግሥት ሰጥቷል።
ይህ ፖሊሲ በተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተኮንኗል።
ከ2013 ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ጠያቂዎች በማቆያዎች ተይዘዋል። ጥያቄያቸው እስኪገመገም ድረስ ለዓመታት በዛው ከመቆየት ውጪ አማራጭ የላቸውም።