ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል በጋዛ ያወደመችው ሕንፃ የሚሳኤል መከላከያዋን የሚያጠቃ ተግባር ተፈጽሞበታል አለች
በቅርቡ በጋዛ በነበረው ግጭት እስራኤል ባካሄደችው የአየር ድብደባ ያወደመችው ሕንፃ፤ የሃማስ ታጣቂ ቡድን የሚሳኤል መቃወሚ ሥርዓቷን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ሙከራዎች ያከናውንበት ነበር ስትል አስተባበለች።
የጃላ ግንብ በመባል የሚታወቀው ይህ ሕንፃ የአሶሺየትድ ፕረስ እና የአል ጀዚራ ቢሮዎችን የያዘ ነበር።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር በኒው ዮርክ በሚገኘው አሶሺየትድ ፕረስ (ኤፒ) ቢሮ በመገኘት ስለ ጥቃቱ ያስረዱ ሲሆን፤ ቢሮዎቹን መልሶ ለመገንባት እገዛ ለማድረግ ጥያቄ አቅርበዋል።
ኤፒ ስብሰባውን መቀበሉን ቢገልጽም እስራኤል ያለችውን የሚያስደግፍ ማስረጃ ግን እስካሁን አላቀረበለችልኝም ብሏል።
ጋዛን የሚቆጣጠረው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ የእስራኤልን ክስ አስመልክቶ እስካሁን ድረስ የሰጠው አስተያየት የለም።
በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት፤ ሃማስ እና እስራኤል ለአሥራ አንድ ቀን ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ 256 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከነዚህም ውስጥ ቢያንስ 128 የሚሆኑት ሰላማዊ ዜጎች በጋዛ የተገደሉ ናቸው።
የእስራኤል ጦር ኃይል በበኩሉ ከተገደሉት ውስጥ 200 ታጣቂዎች ናቸው ብሏል። በጋዛ የሃማስ መሪ የሆነው ያህያ ሲንዋር በግጭቱ የተገደሉ ተዋጊዎች 80 ናቸው ሲል መግለጹ ይታወሳል።
እስራኤል ሕንፃው ውስጥ በአንድ የሃማስ ክፍል ሲደረግ የነበረውን የጠለፋ ተግባር በተመለከተ የኤፒ ሠራተኞች መረጃው ነበራቸው ብላ እንደማትጠረጥርም አምባሳደሩ አስረድተዋል።
አገራቸው የፕሬስ ነጻነትን እንደምታከብር ገልጸውም፤ ኤፒ በጋዛ ቢሮውን በድጋሚ ለመገንባት ብሎም ቁሳቁሶቹን ለሟሟላት የሚያደርገውን ተግባር ለማገዝ ጥያቄ አቅርበዋል።