በዩኬ የማህፀን በር ካንሰር ክትባት የወሰዱ ወጣት ሴቶችን ከሞት ማትረፍ ተቻለ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዩናይትድ ኪንግደም ከማህፀን በር ካንሰር የሚጠብቅ ክትባት 200 የሚጠጉ ሕይወቶችን ማትረፉን ጥናት አስታወቀ።

በዓይነቱ የመጀመሪያው ነው የተባለው ጥናት እ.አ.አ በ2008 ታዳጊ ተማሪዎች 'ኤችፒቪ' የሚባለው ክትባት ከተሰጣቸው በኋላ በበሽታው የሚከሰተው ሞት ማሽቆልቆሉን አሳይቷል።

ከ2020 እስከ 2024 ባሉ ዓመታት ከ20 እስከ 24 ዓመት ባሉ ሴቶች ላይ አንድም የማህፀን በር ካንሰር ሞት አልተመዘገበም። በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲህ ሲሆን የመጀመሪያው ነው።

ካለ ክትባቱ 23 የሚሆኑ ሴቶች ሕይወታቸው እንደሚያልፍ ተጠብቆ ነበር።

በለንደን ኩዊን ሜሪ ዩኒቨርስቲ መሪ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ፒተር ሳሲኒ "አንድ ነጠላ ክትባት አንድን የካንሰር ዓይነት ለይቶ ሊያስወግድ ይችላል ብሎ ማሰብ አስደናቂ ነው" ብለዋል።

ጥናቱ 12 ወይንም 13 ዓመት የሆናቸው ክትባቱን የወሰዱ ታዳጊዎች ከ30 ዓመታቸው በፊት በበሽታው የመሞት ስጋታቸው ዜሮ መሆኑንም አረጋግጧል።

ከክትባት ዘመቻው በፊት በእዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ በየዓመቱ 20 ሞቶች ይመዘገቡ ነበር።

በዩናይትድ ኪንግደም የማህፀን በር ካንሰር በሴቶች ላይ የተለመደ 14ተኛ የካንሰር አይነት ነው። በየዓመቱ 3,300 ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ በሐኪም ይነገራቸዋል።

ቆዳ በቆዳ ንክኪ የሚሰራጨው የ'ኤችፒቪ' ቫይረስ 99 በመቶ የማህፀን በር ካንሰርን ያስከትለል።

በአብዛኛው ከቫይረሱ ኢንፌክሽኖች ምንም ችግር ሳያስከትሉ ማገገም የሚቻል ቢሆንም አንዳንዶች የህዋስ ለውጥ በማስከተል ከዓመታት በኋላ ወደ ካንሰር ሊያመራ ይችላል።

ተመራማሪዎቹ ክትባት ለብዙዎች በተሰጠ ቁጥር እና የተከተቡ ሰዎች እያደጉ ሲሄዱ በበሽታው የሚመዘገበው የሞት ምጣኔ እያሽቆለቆለ ይሄዳል ብለዋል።

ምርምሩን በገንዘብ የደገፈው የዩናይትድ ኪንግደም የካንሰር ምርምር ተቋም የምርምሩን ግኝቶች "አስደናቂ እርምጃ" ብሎታል። ይሁን እንጂ በዩናይትድ ኪንግደም የክትባቱ ምጣኔ ከሚመከረው በታች ነው ሲል አስጠንቅቋል።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚሼል ሚችል "የማህፀን በር ካንሰር ከመያዙ በፊት በማስቆም የ'ኤችፒቪ' ክትባት በጣም ፍቱን እንደሆነ እናውቃለን። እናም እነዚህ ግኝቶች ሕይወት እያዳነ እንደሆነ አሳይተዋል" ብለዋል።

አሌክሳንዳ ሌግ በዩኬ የ'ኤችፒቪ' ክትባት ከመጀመሩ በፊት ነበር ትምህርቷን ያቋረጠችው።

እ.አ.አ በ2021 ለሰርጓ እየተሰናዳች እያለ ነበር በ30 ዓመቷ በማህፀን በር ካንሰር እንደተያዘች የተነገራት።

ቀዶ ሕክምና ያደረገች ሲሆን ሐኪሞች ከማህፀኗ የተወሰነ ክፍል ማዳን ችለው ነበር። ይህም የማርገዝ እድል ሰጥቷል።

አሌክሳንድራ ከአንድ ዓመት በኋላ ልጇን አይቪን ወልዳለች። ሁለተኛ ስሟንም "ተዓምር" ብላታለች።

ይሁን እንጂ አሌክሳንድራ ክትባቱን አስቀድማ ብታገኝ ኖሮ ሕይወቷ በስጋት እን ጭንቀት አይሞላም ነበር ትላለች። ለዚህም ነው ክትባቱን ለመውሰድ ብቁ የሆኑ ሴቶች ክትባቱን እንዲወስዱ የምታሳስበው።

ፕሮፌሰር ሳሲኒ ክትባቱ መሰጠት ከተጀመረ ወዲህ የሞት ምጣኔ መቀነሱን "የተራራው ጫፍ" ይሉታል።

"የተከተቡ ትውልዶች ሲያድጉ ከማህፀን በር ካንሰር ብዙ ሕይወት ሲተርፍ እናያለን" ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የማህፀን በር ካንሰርን የኅብረተሰብ ጤና ችግር በማለት በ2040 ለማጥፋት ቃል ገብቷል።

ነገር ግን በቅርብ የወጡ መረጃዎች በመላው አገሪቱ ክትባቱ መሰጠት ከሚመከረው ምጣኔ በታች መሆኑን ያሳያሉ።

የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ደኅንነት ኤጄንሲ መረጃ እንደሚያሳው ከ2024 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ 76 በመቶ ታዳጊ ሴቶች በ15 ዓመታቸው ተከትበዋል። ይህም የዓለም የጤና ድርጅት የማህፀን በር ካንሰርን ለማጥፋት ከሚመክረው የ90 በመቶ የክትባት ምጣኔ ያነሰ ነው።

ከክትባቱ ባለፈው ከ26 እስከ 64 ዓመት ያሉ ሴቶች የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል።