ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጆርጅ ፍሎይድ እህት ፕሬዚዳንት ባይደንን አላገኝም አለች
በፖሊሶች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ እህት ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር አልገናኝም በማለት እምቢተኝነቷን አሳይታለች።
የጆርጅ ፍሎይድ አንደኛ አመት ሙት መታሰቢያ ወቅት እህቲቱ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ሊያደርጉት የነበረውን ስብሰባ የሰረዘችው "የገቡትን ቃል አጥፈዋል" በሚል ነው።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የፖሊስ ማሻሻያ ረቂቅ ማፅደቅ አልቻሉም ብላለች።
ብሪጀት ፍሎይድ በሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ የተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገኘች ሲሆን ሌሎች የቤተሰቦች አባላት ደግሞ ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር ተገናኝተው ረቂቁ በሚፀድቅበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
'ዘ ጆርጅ ፍሎይድ ጀስቲስ ኢን ፖሊሲንግ አክት' የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ ረቂቅ ፖሊስ ተጠያቂ የሚሆንበት ፣ በዘር ልዩነት የሚደረጉ እስሮችን ማስቆም፣ በፍትህ ዙሪያ ላይ ያሉ አሉታዊ ነገሮችን መቀየርና በህግ አስፈፃሚና በማህበረሰቡ ላይ ያሉ ግንኙነቶችን መገንባትና መዋቅራዊ ዘረኝነትን መስበር የሚሉ ጉዳዮችን ይዟል።
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ በፖሊሶች አንገቱ መሬት ላይ ተጣብቆ የተገደለው ጆርጅ ፍሎይድ አንደኛ አመት ሙት መታሰቢያ ነው።
የቀድሞ የሚኒያፖሊስ ፖሊስ ዴሬክ ቾቪን በባለፈው ወር ነው በ46 አመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው።
ነጩ ፖሊስ ዴሪክ ቾቪንና የስራ ባልደረቦቹ ጆርጅ ፍሎይድን መሬት ላይ አጣብቀውና ዴሪክም አንገቱ ላይ ለዘጠኝ ደቂቃ አንበርክኮ በመደፈቅ ገድለውታል።
ጆርጅ ፍሎይድ ሃሰተኛ 20 ዶላር ይዟል በሚል ጥርጣሬ ነው ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ያዋሉት።
በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ዴሪክ ከወር በኋላ የሚፈረድበት ሲሆን አርባ አመትም እስር ይጠብቀዋል ተብሏል።
ፕሬዚዳንት ባይደን የፖሊስ ማሻሻያው ረቂቅ ለመፈረም ይዘውት የነበረው ቀነ ገደብ ማክሰኞ እለት አለፈ።
ፕሬዚዳንት ባይደንና ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስን በዋይት ሃውስ ካገኘ በኋላ የጆርጅ ፍሎይድ ወንድም ፊሎኒዝ ለጋዜጠኞች እንደተናገረው "ወፎችን ለመጠበቅ የፌደራል ህግ ማውጣት ከተቻለ ጥቁር ሰዎችን ለመጠበቅ ፌደራል ህጎችን ማርቀቅ ይቻላል" ብሏል።
ሆኖም የነበራቸውንም ስብሰባ አመርቂ ብሎታል። ብሪጀት ፍሎይድ በበኩሏ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በዋሽንግተን የነበራትን ስብሳባ የሰረዘችበትን ምክንያት ተናግራለች።
"ዋሽንግተን ዲሲ ልሄድ የነበረው ባይደን ረቂቁ ላይ ይፈርማሉ በሚል ነው። ባይደን ረቂቁ ላይ አልፈረሙም። ቃላቸውንም አጥፈዋል" ብላለች።
ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው የጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰቦችን ካገኙ በኋላ ለረቂቁ የሚያደርጉትን ድጋፍ እቀጥላለሁ ብለዋል።