የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚደንት በቢሊየን ዶላሮች የጦር መሣሪያ ግዥ ስምምነት ጥፋተኛ አይደለሁም አሉ

የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ እአአ ከ1990ዎቹ ጀምሮ በ5ቢሊየን ዶላር የጦር መሣሪያ ግዥ ላይ በተፈጸመ የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ አይደለሁም አሉ።

የቀድሞ ፕሬዚደንቱ በሙስና ፣ በገንዘብ ማጭበረበር ፣ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በታክስ ማጭበርበርና በሕገ ወጥ ንግድ 16 ክሶች ቀርቦባቸዋል።

ዙማ ግን እዚህ ችግር ውስጥ የከተቱኝ አገሪቷን እያስተዳደረ ባለው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ( ኤኤንሲ) ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ባላንጣዎቼ ናቸው ይላሉ።

የጦር መሣሪያ ግዥ ስምምነቱ አዲስ ተዋጊ ጀት ፣ ሄሊኮፕተር፣ ሰርጓጅ መርከቦችና የጦር መርከቦች ግዥን ያካትታል።

ይሁን እንጅ የግዥ ስምምነቱ ከተፈረመ ከወራት በኋላ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር። አንዳንዶች መንግሥት ይህንን ያህል ገንዘብ ማዋል የነበረበት ለጦር መሣሪያ ግዥ ሳይሆን ድህነትን ለመዋጋት ነበር ሲሉ ትችት ሰንዝረዋል።

በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ዕለት በክዋዙሉ ናታል ግዛት በፔተርማሪዝበርግ ከተማ በሚገኘው ፍርድ ቤት ደጅ ደጋፊዎቻቸው የቀድሞ ፕሬዚደንቱን ለማጽናናት ተሰባስበው ነበር። ፕሬዚደንት ጃኮብ አሁንም የተወሰነ ድጋፍ አላቸው።

የቀድሞ ፕሬዚደንቱ ተከላካይ ቡድን ክስ የመመስረት መብት የለውም በሚል ምክንያት የመንግሥት ዐቃቤ ሕግ የሆኑት ቢሊ ዳውነር ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ጠይቀዋል።

ነገር ግን ሰብሳቢው ዳኛ ጉዳዩ በሐምሌ 19 እንዲታይ ውሳኔ አስተላልፈዋል።

ጃኮብ ዙማ እአአ ከ2009 እስከ 2018 ድረስ ደቡብ አፍሪካን በፕሬዚደንትነት መርተዋል።

በ2018 የቀረበባቸውን የሙስና ክስ ተከትሎ ጃኮብ ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ተገደዋል።

ተተኪያቸው ሲሪል ራማፎሳ ወደ ሥልጣን የመጡት የሙስና መረቡን እበጣጥሳለሁ በሚል ቃል ገብተው ነበር።