ኮሮናቫይረስ፡ በኮቪድ-19 በጠና የታመሙ አፍሪካውያን የመሞት ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን ጥናት አመለከተ

አጥኝዎቹ በ10 የአፍሪካ አገሮች በሚገኙ 64 ሆስፒታሎች ከ3 ሺህ በላይ ህሙማንን ተመልክተዋል፡፡

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አጥኝዎቹ በ10 የአፍሪካ አገሮች በሚገኙ 64 ሆስፒታሎች ከ3 ሺህ በላይ ህሙማንን ተመልክተዋል
ታትሟል

አፍሪካ ውስጥ ከኮቪድ -19 ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ህመም ምክንያት በሆስፒታል የሚታከሙ ሰዎች ከሌላው የዓለም ክፍል በበለጠ የመሞት ዕድል እንዳላቸው አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

ጥናቱ የሕክምና መሣሪያዎች እጥረትን ዋነኛ ምክንያት ነው ብሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እጥረት እና የመሣሪያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር በጥናቱ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡

አጥኝዎቹ ጥናቱ ጽኑ ህመምተኞች ውስን የባለሙያና የሕክምና ቁሳቁስ ባለባቸው አካባቢዎች የሚስተናገዱበትን መንገድ ለማሳወቅ እንደሚረዳ ተስፋ አድርገዋል፡፡

በአፍሪካ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ በኮቪድ -19 ምክንያት ሕይወታቸው የሚያልፍ ህመምተኞች መጠን ከፍተኛ ቢሆንም በአህጉሩ በቫይረሱ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ከዓለም ሕዝብ 17 በመቶውን የምትይዘው አፍሪካ በኮቪድ-19 ምክንያት ከተመዘገበው ሞት 4 በመቶውን ትይዛለች።

አጥኝዎቹ ዘ ላንሴት ሜዲካል ጆርናል ላይ ለታተመው ለዚህ ጥናት በ10 የአፍሪካ አገሮች በሚገኙ 64 ሆስፒታሎች ከ3 ሺህ በላይ ህሙማንን ተመልክተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከፍተኛ እርዳታ የሚፈልጉት ግማሽ ያህሉ የሞቱ ሲሆን፤ የተቀረው ዓለም አማካይ ከአንድ ሦስተኛ በታች መሆኑን ተገንዝበዋል።

የምርምር ቡድኑ መሪ እና የደቡብ አፍሪካው የኬፕታውን ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ብሩስ ቢካርድ "በሃብት ውስንነት ምክንያት ከሌላው ክልል በበለጠ አፍሪካ ውስጥ የሞት ምጣኔው ከፍ ያለ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ኒውስዴይ ፕሮግራም ተናግረዋል፡፡

"ከፍተኛ ሕክምና እንዲያገኙ ከሚላኩት ሁለት ህመምተኞች አንዱ ብቻ ሕክምናው ያገኛል፡፡ እዚያም ከደረሱ በኋላ የሚሰጣቸው ሕክምና ከደረጃ በታች ነው፡፡" ብለዋል ቡድን መሪው።

አንዳንዴም ያሉት አቅርቦቶች በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን አጥኝዎቹ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

"68 በመቶ የሚሆኑት ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት አገልግሎት መስጫ ቢኖራቸውም አገልግሎቱን ማግኘት የቻሉ 10 በመቶ የሚሆኑት ታካሚዎች ብቻ ናቸው" ሲሉ የኡጋንዳው ማኬሬሬ ዩንቨርስቲ ባልደረቦች ዶ/ር ብሩስ ኪሬንጋ እና ፓውሊን ብያኪካ-ኪበዊካ በጥናቱ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የሕክምና መሣሪያዎችን በአግባቡ የሚጠቀሙ ባለሙያዎች አለመኖርን እና የጥገና ችግር መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ሆስፒታል የሚሠሩት ፕሮፌሰር ቢካርድ እንዳሉት የጥናቱ ግኝቶች በዓለም ዙሪያ ክትባቶችን በማከፋፈል ረገድ የሚታየውን አለመመጣጠን እንዲስተካከል የሚገፋፋ ነው።

"በአሁኑ ወቅት አነስተኛ ሃብት ካለን ማተኮር ያለብን ክትባቶችን ላይ ነው፤ ምክንያቱም ክትባቶች ከባድ ህመም እንዳይኖር ስለሚያግዙ ነው" ሲሉ ፕሮፌሰር ቢካርድ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡