ህንድ ቅዱስ በምትለው ወንዝ በርካታ የኮሮና ህሙማን አስከሬኖች ተጥለው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ህንድ ቅዱስ ብላ የምትጠራው ጋንጀስ ወንዝ በበርካታ አስከሬን መጥለቅለቁ ተሰምቷል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ አስከሬኖች በወንዙ ላይ ሲንሳፈፉ እንዲሁም በባህር ዳርቻው በሚገኙ አሸዋዎች ላይ ተዘርግተው ታይተዋል።
በሰሜናዊ ኡታር ፕራዴሽ ግዛትና በወንዙ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በወንዙ ተጠርገው የተወሰዱት አስከሬኖች በኮሮናቫይረስ ህመም ህይወታቸው ያለፈ ነው ይላሉ።
ኒራጅ ኩማር ሲንግ የተባሉ የግዛቲቷ የፖሊስ ዋና ተቆጣጣሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በባህር ዳርቻው ላይ የተገኙትን አስከሬኖች የዲኤንኤ (ዘረ መል ) ምርመራ መደረጉን ነው።
ባለስልጣናቶቹ እንደሚሉት አንዳንዶቹ አስከሬኖች የሰውነት ክፍሎች ሲሆኑ ይህም በአካባቢው በሚደረገው የአስከሬን ቃጠሎ (ክሪሜሽን) ጋር የተገናኘ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ነገር ግን በአብዛኛው እነዚህ አስከሬኖች ሆን ተብለው ወደ ወንዙ የተጣሉ እንደሆኑ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ፖሊስ በውሃው ዙሪያም መረብ ቢያጥርም በአሁኑ ወቅት በርካታ አስከሬኖች መገኘታቸው አልቀረም። በባህር ዳርቻው የሚገኙ አስከሬኖችን ውሾችና አሞራዎች ሲቀራመቷቸውም ታይቷል።
በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተመታችው ህንድ በተለይም በባለፉት ሳምንታት የተነሳው ሁለተኛው ወረርሽኝ ከቁጥጥር ውጭ ነው ተብሏል።
እስካሁን ባለው መረጃ 25 ሚሊዮን የኮሮናቫይረስ ህሙማንን የመዘገበች ሲሆን 275 ሺህ ዜጎቿንም በቫይረሱ አጥታለች።
ነገር ግን በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የሟቾች ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ነው።
በባህር ዳርቻ ተጥለው የተገኙ አስከሬኖች፣ በህንድ እንደሚደረገው የአስከሬን ማቃጠያ ቦታዎች ማጣት የሟቾች ቁጥር ይፋዊ ከሆነው በላይ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።
ቢቢሲ በቫይረሱ ክፉኛ በተጠቃችው ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ያናገራቸው የአካባቢው ጋዜጠኞች፣ ባለስልጣናትና የአይን እማኞች እንዳሉት ከነዚህ ከሚንሳፈፉ አስከሬኖች ጀርባ ባህላዊ እምነቶች፣ ድህነትና ወረርሽኙ በብርሃን ፍጥነት ምን ያህል ሰዎችን እንደቀጠፈ ማሳያ ነው ይላሉ።












