ኮቪድ-19፡ በኢንግላንድ፣ ዌልስና እና በአብዛኛው ስኮትላንድ የእንቅስቃሴ ገደብ ላላ

የተቃቀፉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ታትሟል

በኢንግላንድ፣ ዌልስ እና በአብዛኛው የስኮትላንድ አካባቢ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ መላላቱ ተገለጸ።

ይህንን ተከትሎ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ሰዎች የራሳቸውን ድርሻ መወጣታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አሁን ላይ ሰዎች ቁጥራቸውን በመወሰን በቤት ውስጥ መሰባሰብና ማሕበራዊ ግንኙነታቸውን ማካሄድ፣ የሚወዱትን ሰው ማቀፍ፣ መጠጥ ቤቶችና ምግብ ቤቶች ጎራ ማለት ይችላሉ ተብሏል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ የሚደረግ ጉዞ ላይ የተጣለው ገደብም ተነስቶ በሌላ ሕግ ተተክቷል።

ይሁን እንጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ማንኛውም ሰው ጥንቃቄ ማድረግና በሳምንት ሁለት ጊዜ መመርመር እንዳለበት ተናግረዋል።

"ከእንቅስቃሴ ገደቡ ለመውጣት አንድ ላይ ሆነን ብዙ ርቀት ተጉዘናል፤ ይህንን ቀጣይ እርምጃ በጥንቃቄ መውሰድ አለብን" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ አክለውም እያንዳንዱ ሰው በሳምንት ሁለት ጊዜ ምርመራ በማድረግ፣ ክትባቱን በመውሰድ የድርሻውን ሚና መወጣት አለበት ብለዋል።

ሰዎች አዲስ የተሰጠውን ነጻነት ሲያጣጥሙ ጥንቃቄና ኃላፊነት በተሞላበት እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥብቅ አሳስበዋል።

በኢንግላንድ እና ስኮትላንድ ያለ ማንኛውም ሰው ምንም የበሽታው ምልክት ባይታይበትም ውጤቱን በ30 ደቂቃ ማወቅ የሚያስችል ነጻ ምርመራ ማድረግ ይኖርበታል።

በዌልስ እና በሰሜን አየርላንድ ግን ምርመራው ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተፈቀደ ነው። ለምሳሌ ከቤት ሆነው መስራት ለማይችሉ ሰዎች።

በወረርሽኙ ሳቢያ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ በኢንግላንድ፣ በስኮትላንድና ዌልስ እንዲላላ ቢደረግም በእያንዳንዱ አካባቢ የተደረጉ ለውጦች ግን የተለያዩ ናቸው። በስኮትላንድ የሚገኙት ግላስጎው እና ሞራይ አካባቢ የወረርሽኙ ሥርጭት በመጨመሩ የተጣለው ገደብ ባለበት ይቆያል።

አዲሱ መመሪያ ምን ይላል?

ኢንግላንድ:

• በቤት ውስጥ እስከ ስድስት የሚደርሱ ሰዎች ወይም ሁለት ቤተሰቦች በቡድን ሆነው መገናኘት ይችላሉ። እስከ 30 የሚደርሱ ሰዎች ከቤት ውጭ መሰባሰብ የሚችሉ ሲሆን ምሽቱን ማሳለፍም ተፈቅዷል።

• የመጠጥ መደብሮች፣ መጠጥ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች ደንበኞችን በቤት ውስጥ ማስተናገድ ይችላሉ።

• ቤተ መዘክሮች፣ ፊልም ቤቶች፣ የሕጻናት መጫዎቻ ቦታዎች፣ ትያትር ቤቶች፣ የሙዚቃ ድግሶች እና ስታዲየሞች ልክ እንደ ሆቴሎች ሁሉ መከፈት ይችላሉ።

• ማሕበራዊ ርቀትን መጠበቅ የተመለከተው መመሪያም ተለውጧል። ከሌላ ቤተሰብና ወዳጅ ጋር መተቃቀፍ ግላዊ ምርጫ ነው ተብሏል።

ስኮትላንድ (ከግላስጎው እና ሞራይ በስተቀር)፡

• ቁጥራቸው እስከ ስድስት የሚደርሱ ሰዎች ወይም እስከ ሦስት የሚደርሱ ቤተሰቦች በቤት ውስጥ መሰባሰብ ይችላሉ። ከቤት ውጭ ደግሞ እስከ ስምንት የሚደርሱ ከስምንት ቤተሰብ ውስጥ የተውጣጡ ሰዎች መቀላቀል ይችላሉ።

• የመጠጥ መደብሮች እና ምግብ ቤቶች በቤት ውስጥ እስከ ምሽቱ 4፡30 ድረስ የአልኮል መጠጦች መሸጥ ይችላሉ።

• እንደ ፊልም ቤቶች፣ ትያትር እና ቢንጎ መጫወቻ አዳራሾች እስከ 100 የሚደርሱ ሰዎችን በቤት ውስጥ ማስተናገድ ይችላሉ።

ዌልስ፡

• የመጠጥ መሸጫ ቤቶችና ምግብ ቤቶች በቤት ውስጥ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ። በእነዚህ ቦታዎች እስከ ስድስት ከሚደርሱ ቤተሰቦች የተሰባሰቡ እስከ ስድስት የሚደርሱ ሰዎች መገናኘት ይችላሉ።

• ሁሉም የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያና ማረፊያ ቦታዎች መከፈት ይችላሉ።

• ፊልም ቤቶች፣ የባውሊንግ ጨዋታዎች፣ ቤተ መዘክሮች፣ ጋለሪ እና ትያትር ቤቶች መከፈት ይችላሉ።

• በቤት ውስጥ በመሰባሰብ በሚደረጉ ማሕበራዊ ግንኙነቶች ላይ ግን ለውጥ የለም። ይህ አሁንም የተከለከለ ሲሆን የቅርብ ግንኙት ከሌላቸው ሁለት ቤተሰቦች መሰባሰብና አካላዊ ንክኪ ማድረግ የተከለከለ ነው።

በሦስቱም አገራት እንደ ካርኒቫል ያሉ ከአገር ውጭ የሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ መታደም የተፈቀደ ነው። ሰሜን አየርላንድ የእንቅስቃሴ ገደብ መመሪያዋን እየተመለከተች ሲሆን የተወሰኑት ከቀናት በኋላ ሊነሱ እንደሚችሉ ተስፋ ተደርጓል።