ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኬንያ ምክር ቤት አባል በፓርላማው ድምጽ ለመስጠት 1ሺህ ዶላር ጉቦ መቀበላቸውን አመኑ
በኬኒያ የሕዝብ እንደራሴ የሆኑት ሞሰስ ኩሪያ ባለፈው ዓመት የምክር ቤቱን የአብላጫ መቀመጫ ያለውን ፓርቲ መሪ ለመምረጥ 1000 የአሜሪካ ዶላር ወይም 100 ሺህ የኬኒያ ሽልንግ መቀበላቸውን ለቢቢሲ ገለፁ።
"በምክር ቤት አባላት ዘንድ እንዲህ ያለ የማበረታቻ ክፍያ መቀበል አዲስ ነገር አይደለም" በማለት ድርጊቱን የገለፁት ሲሆን አስፈላጊ ከሆነም ገንዘቡን ለመመለስ ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
ኩሪያ ይህንን የገለፁት ከሁለት ባልደረቦቻቸው ጋር ከሰሞኑ አገራቸው ያካሄደችውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ለመደገፍ የእጅ መንሻ ተቀብላችኋል የሚሉ ክሶች እየተሰሙባቸው ባለበት ግዜ ነው።
አብላጫ ያለው ፓርቲ መሪ አሞጽ ኪሙኒያ በበኩላቸው በምክር ቤቱ ውስጥ ተከፍለዋል የተባሉትን ጉቦዎች ክደዋል። ቢቢሲም የኩሪያን ክስ ለኪሙኒያ ቢያቀርብላቸውም እስካሁን ድረስ መልስ አልሰጡም።
የኬኒያ የምክር ቤት አባላት በዓለም ላይ ከፍተኛ ተከፋይ ከሚባሉት ዝርዝር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ኬንያ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ በሙስና እንደምታጣ ይገመታል።
ኩሪያ በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ለበርካታ ግዜያት ሙስና መመልከታቸውን ገልፀዋል።
"ለስምንት ዓመታት የምክር ቤት አባል ሆኜ በቆየሁባቸው ግዜያት ቆጥሬ የማልጨርሰውን ያህል ግዜ ይህንን ድርጊት ተመልክቻለሁ" ሲሉም ለቢቢሲ ኒውስ ዴይ ፕሮግራም ተናግረዋል።
"እነዚህ ነገሮች በርግጥ በካሜራ ፊት ለፊት አይካሄዱም" ሲሉም አክለዋል።
ለዚህም ምሳሌ አድርገው የአብላጫ መሪውን ኪሙያን ሹመት የጠቀሱ ሲሆን ከዓመት በፊት በተደረገው ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነበር ይህንን ሹመት ያገኙት።
"ትክክል አይደለም። እድሉ ካለ ቢያንስ በደንብ ያማስታውሰውን ክፍያ ለመመለስ ፈቃደኛ ነኝ" ሲሉ ተደምጠዋል።
"ዛሬም ቢሆን ለመመለስ ፈቃደኛ ነኝ፤ አሞስ ኪሙያን የአብላጫ መሪ አድርጌ ለመምረጥ የተቀበልኩትን 1000 ዶላር ማለቴ ነው" ብለዋል።
ኩሪያ አወዛጋቢ ሆኖ በቆየው የሕገ መንግስት ማሻሻያ ላይ የድጋፍ ድምጽ ለመስጠት አንዳንድ ፖለቲከኞች 1000 ዶላር ሙስና ተቀብለዋል ማለታቸውን ተከትሎ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ነገሩን እንዲያብራሩ መጥሪያ ልከውላቸዋል።
የሕገ መንግሥት ማሻሻያው በፕሬዘዳንቱ ብሎም በተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ የሚደገፍ እና አገሪቱ ከነፃነት በኋላ የገጠሟትን እንደ ሙስና እና የዘር ጥላቻ ያሉ ችግሮችን ይቀንሳል የተባለለት ነው።
የሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያው ተቃዋሚዎች በበኩላቸው የምክር ቤት አባላትን መቀመጫ በመጨመር፣ ከዚህ በፊት ተቀንሶ የነበረውን የጠቅላይ ሚኒስትር ቦታን ብሎም በርካታ ምክትሎችን ለመምረጥ የሚያስችል በመሆኑ የመንግሥትን ወጪ ብሎም ብክነትን ይጨምራል ሲሉ ይከራከራሉ።
ታዲይ ኩሪያ የዚህን ማሻሻያ የሚቃወሙት ምክትል ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ ደጋፊ ናቸው። ሩቶ የተቃዋሚው ኦዲንጋ ጠንካራ ተፎካካሪም ሲሆኑ ፕሬዘዳንት ኡሁሩን ለመተካት በቀጣይ አመት በሚደረገው ምርጫ ላይ ይፎካከራሉ።
ምንም እንኳን ይህ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ከፍተኛ ተቃውሞ ቢገጥመውም በየክፍለሃገሩ ምክር ቤቶች ብሎም በፓርላማው ፀድቋል።
ኩሪያ የሕገ መንግስት ማሻሻያውን ለማድረግ የተከፈሉ የእጅ መንሻዎች በፓርላማው ውስጥ ብቻ አያበቁም ያሉ ሲሆን የክፍለ ሃገራቱ የምክር ቤት አባላትም መደለያውን ተቀብለዋል ብለዋል።