ኮሮናቫይረስ፡ በዩኬ እስከ 10ሺህ ተመልካቾች ወደ ስታዲየም እንዲገቡ ሊፈቀድ ነው

የፎቶው ባለመብት, David Price
እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ደጋፊዎች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በእግር ኳስና ሌሎች ሜዳዎች ተገኝተው የሚደግፉትን ቡድን ማበረታታት እንደሚችሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አስታወቁ።
በዚህም መሰረት በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዓመት ቡድኖች የሚያድርጓቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ደጋፊዎች ገብተው መመልከት ይችላሉ ማለት ነው።
''ወደ ስታዲየም የሚገቡትን ሰዎች ቁጥር ቀነስ አድርገን የስታዲየሞቻችንን በሮች መክፈት እንጀምራለን'' ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ምሽት ባስተላለፉት መልዕክት።
''ደጋፊዎቸ በስታዲየሞቻችን በጣም ተናፍቀው ነበር፤ ፕሪምየር ሊጉም ቢሆን ያለእነሱ ቀዝቀዝ ብሏል። የደጋፊዎች መመለስ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት መጨረሻ ያሳምረዋል'' ብለዋል።
ካሳለፍነው ታህሳስ ወር ጀምሮ በአንዳንድ ስታዲየሞች እስከ 2 ሺህ የሚደርሱ ደጋፊዎች ገብተው እንዲመለከቱ ተፈቅዶ የነበረ ሲሆን በአገሪቱ የተቀሰቀሰውን አዲስ የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ ተመልሶ ተቋርጧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 10 ሺህ ተመልካቾች ተገኝተው ጨዋታዎችን መመልከት ይችላሉ ከማለታቸው በፊት በካራባዎ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ እና ቶተንሃም ያደረጉት ጨዋታ ላይ ለሙከራ ተብሎ 2 ሺህ ተመልካቾች ገብተው እንዲመለከቱ ተደርጎ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአዲሱ መመሪያ መሰረት በትልልቅ ስታዲየሞች እስከ 10 ሺህ ተመልካቾች አልያም ስታዲየሙ መያዝ ከሚችለው 25 በመቶ የተፈቀደ ሲሆን በአነስተኛ ስታዲየሞች ደግሞ 50 በመቶ ወይም እስከ 4 ሺህ የሚደርሱ ተመልካቾች ገብተው እንዲታደሙ ተብሏል።
የቤት ውስጥ ሜዳዎች ደግሞ እስከ 1 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን ወይም መያዝ ከሚችሉት 50 በመቶውን ብቻ አገልግሎት ላይ እንዲያውሉ ተወስኗል።
ባለፈው ዓመት የኮሮናቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ከመጋቢት ወር ጀምሮ እንግሊዝ ውስጥ የሚካሄዱ አብዛኞቹ የእግር ኳስ ውድድሮች በዝግ ስታዲየሞች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ በስታዲየሞች ገብተው የሚመለከቱ ደጋፊዎችን ቁጥር እስከ 21 ሺህ ድረስ ከፍ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን በዛውም አብዛኛዎቹ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንደሚነሱ ይጠበቃል።
በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ደግሞ የሙከራ ስራዎቹ ቀጥለው በኤፍኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ቼልሲ እና ሌስተር ሲቲተ ሲገናኙ እስከ 21 ሺ የሚደርሱ ደጋፊዎች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።












