ካናዳ ፋይዘር የተሰኘው ክትባት ለሕፃናት እንዲሰጥ ፈቀደች

የኮሮናቫይረስ ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ካናዳ ፋይዘር የተሰኘውን የኮሮናቫይረስ ክትባት ከ12 እስከ 15 ዓመት ላሉ ህጻናት እንዲሰጥ ፈቃድ ሰጠች።

ይህ ውሳኔ የኮሮናቫይረስ ክትባት በዚህ ዕድሜ ላሉ ህጻናት እንዲሰጥ የፈቀደች የመጀመሪያዋ ሀገር አድርጓታል።

የሶስተኛ ምዕራፍ ‘የክሊኒካል’ ሙከራ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ነው የሃገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ፋይዘር የተሰኘው ክትባትከ 12 እስከ 15 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ያሉ ህጻናት እንዲከተቡ ይሁንታውን የሰጠው።

“በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ላይ የተሞከረው ክትባቱ አስተማማኝና ውጤታማ ነው” ሲሉ የሚኒስቴሩ አማካሪ ገልጸዋል።

ፋይዘር ቀደም ብሎ በሀገሪቱ ከ16 ዓመት በላይ ያሉ ሰዎች እንዲወስዱት ካናዳ ፈቅዳ ነበር።

በሀገሪቱ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ በሆነባት የአልቤርታ ግዛት ከ9 ቀናት በኃላ ከ12 እስከ 15 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ታዳጊዎች ክትባቱን መውሰድ ይጀምራሉ።

በካናዳ እስካሁን 1.2 ሚሊዮን ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የያዛቸው ሲሆን 20 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ19 ዓመት በታች ነው።

የክትባት አሰጣጡ በአንጻራዊነት የዘገየ እንደሆነ በሚነገርባት ካናድ 34 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ቢያንስ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ወስዷል።