ቤልጂዬማዊው ገበሬ በስህተት ሁለቱን ሃገራት የሚለውየውን ድንበር ገፋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቤልጂዬም ውስጥ ያለ አንድ አራሽ በስህተት ሃገሩ ከፈረንሳይ ጋር የምትዋሰንበትን መስመር መግፋቱ አጀብ አሰኝቷል።
አንድ የታሪክ ተመራማሪ ነው በፈረንሳይና ቤልጂዬም አዋሳኝ ድንበር አቅራቢያ ካለ ዱር ሲንሸራሸር ሁለቱን ሃገራት የሚለየው ድንጋይ 2.29 ሜትር መገፋቱን ያየው።
ቤልጂዬማዊው ገበሬ ድንበር የሚለየውን ድንጋይ የገፋው ድንጋዩ ማረሻ 'ትራክተሩ' ውስጥ ገብቶ ስለተሰነቀረበት በተሰማው ብስጭት ነበር።
ፈረንሳይና ቤልጂዬም በዚህ ጉዳይ ድንበር ይገባኛል ሲሉ ነፍጥ አላነሱም። ይልቁንስ የሁለቱም ሃገራት ሰዎች የገበሬውን ድርጊት እያነሱ ተሳስቀዋል።
"ገበሬው ቤልጂዬምን አተልቆ ፈረንሳይን አሳንሷታል። ይህ መልካም አይደለም" ሲሉ የቤልጂዬሟ ኤርኩዌሊንስ አውራጃ አስተዳዳሪ ለፈረንሳዩ ተሌቪዥን ጣቢያ ቲኤፍ1 ተናግረዋል።
620 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የፈረንሳይና ቤልጂዬም ድንበር በፈረንጆቹ 1820 ነው የተሰመረው።
የኮርትሪክ ስምምነት እየተባለው የሚጠራው የሁለቱ ሃገራት ድንበር መስመር ይፋ የሆነው ኖፓሌዎን በዋተርሉ አምባ ከተሸነፈ በኋላ ነው።
አስተዳዳሪው የድንበር ጉዳይ እንኳን ሁለት ጎረቤት ሃገራትን ይቅርና በሁለት ሰዎች መካከል ግጭት ሊቀሰቀስ ቢችልም እኛ ግን አይነካካንም ሲሉ ተደምጠዋል።
"የኔ አውራጃ ተለቅ በማለቱ ደስ ብሎኛል" ሲሉ በፈገግታ ተሞልተው ነበር የተናገሩት።
የፈረንሳይዋ ጎረቤት አውራጃ ኦሬዬ ዌሎኔክ በበኩላቸው "በአሁኑ ወቅት መቼም ሌላ የድንበር ጦርነት ውስጥ አንገባም" ሲሉ ነገሩን በፌዝ አልፈውታል።
ገበሬው ድንጋዩን ካነሰባት ቦታ እንዲመልስና የሁለቱን ሃገራት ድንበር እንዲያቀና ተጠይቋል።
ሰውዬው እምቢኝ ካለ ግን ጉዳዩ ወደ ቤልጂዬም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሊያመራ ይችላል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የፍራንኮ-ቤልጂያን የድንበር ኮሚሽን ሰዎችን ጠርቶ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል።
የሁለቱን ሃገራት ድንበር ጉዳይ የሚመለከተው ኮሚሽን ከፈረንጆቹ 1930 ጀምሮ ይህን ያህል የተጋነነ ጉዳይ ገጥሞት አያውቅም።












