ኬንያ በፖሊሶች መካከል የሚኖረውን የፍቅር ግንኙነት ለመከልከል አቀደች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኬንያ በፖሊስ መኮንኖች መካከል የሚኖረውን የፍቅር ግንኙነት ለመከልከል ማቀዷ ተሰማ።
የአገሪቷ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በፖሊስ ኮሌጅ በተዘጋጀና በቴሌቪዥን በተላለፈ ፕሮግራም ላይ እንዳሉት የዚህ እቅድ ዓላማ በፖሊስ መኮንኖቹ መካከል የሚፈፀመውን ከፍተኛ ወንጀል መቀነስ ነው።
የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፍሬድ ማቲያንጊ እቅዱን ተፈጻሚ ለማድረግ በቅድሚያ ለብሔራዊ ጸጥታ ምክር ቤት ይቀርባል ብለዋል።
ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤቱ በአገሪቷ ያለውን ጠቅላላ የጸጥታ ኃይል ከበላይ ሆኖ የሚቆጣጠር አካል ነው።
በአገሪቷ ጦር በተለያየ ደረጃ በሚገኙ የጦር መኮንኖች መካካል የሚደረግ የፍቅር ግንኙነት ክልክል መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።
ባለፉት ጥቂት ወራት በፖሊስ መኮንኖች ውስጥ የትዳር አጋር ግድያ መጨመሩን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
“ከዚህ በኋላ ይህንን ቁጭ ብለን ማየት አንችልም፤ በጸጥታው ዘርፍ ያሉትን ተግዳሮቶችም ችላ ብለን አናይም” ብለዋል ሚኒስትር ማቲያንጊ።
የሥርዓተ ጾታ ላይ የሚሰራው መሥሪያ ቤትም በሴት ፖሊሶች የቀረበውን የወሲባዊ ትንኮሳ ክስ እንደሚመለከተውገልጿል።
ዘ ስታር ጋዜጣ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጠቅሶ እንደዘገበው “ በቀጣይ አንድ የፖሊስ መኮንን ከሌላ የሕግ አስፈጻሚ መኮንን ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመርም ሆነ መጋባት ሕገ ወጥ ይሆናል።
ምን አልባት ሁለት ፖሊሶች በፍቅር ከወደቁ አንደኛቸው ሥራቸውን የግድ መልቀቅ ይኖርባቸዋል “ ብለዋል።












