ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮቪድ-19፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፉን የኮቪድ-19 የይለፍ መተግበሪያን መጠቀም ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆነ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፉን የኮሮናቫይረስ የይለፍ መተግበሪያ [አፕ] በመጠቀም ከአፍሪካ የመጀመሪያው መሆኑ ተገለጸ።
አየር መንገዱ በድረ ገጹ ላይ እንዳስታወቀው በዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (አያታ) የተዘጋጀውን የዲጂታል የይለፍ መተግበሪያን በመቀበል በአፍሪካ ካሉ አየር መንገዶች የመጀመሪያው ሆኗል።
ይህ መተግበሪያ የኮሮናቫይረስ ውጤትን ብሎም የክትባት ሁኔታን ለመለየት ያግዛል።
መተግበሪያው ተጓዦችን፣ አየር መንገዱን፣ ላቦራቶሪዎችን ብሎም መንግሥትን በማቆራኘት ትክክለኛ የኮሮናቫይረስ የምርመራ ውጤት በጉዞ ወቅት መቅረቡን የሚያረጋግጥ ነው።
ይህም ተጓዦች የኮሮናቫይረስ ውጤታቸውን ብሎም የክትባት ማረጋገጫቸውን ቀድመው የሚያይዙበት ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን የዲጂታል የይለፍ ሥርዓት በአራት የተለያዩ ዓለም አቀፍ በረራዎች ላይ ከሁለት ቀናት በፊት መተግበር እንደጀመረ በድረ-ገጹ ላይ ይፋ አድርጓል።
አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ እና ቶሮንቶ እንዲሁም ከለንደን እና ከቶሮንቶ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጋቸው በረራዎች ላይ ሙከራውን እንደሚያካሂድ አስታውቋል።
የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት አካላዊ ንክኪን ለማስወገድ በሁሉም አሠራሩ ዲጂታል መሆኑን የገለጸው አየር መንገዱ፤ ይህም መንገደኞች ልዩ በሆነው የበረራ ልምዶቻቸው እንዲደሰቱ ያስችላቸዋል ብሏል።
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ዓለም አቀፍ ወረርሽኙ እያደረሰ ያለውን ችግር ለመጋፈጥ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።
"በሙሉና በጥንቃቄ የአየር በረራ ለመጀመር ይህን አዲስ የዲጂታል የይለፍ መተግበሪያ ለደንበኞቻችን በማቅረባችን ደስተኞች ነን" ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ መንገደኞች በዲጂታል የይለፍ መተግበሪያውን በመጠቀም ውጤታማ፣ ከንክኪ ነጻ የሆነ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ጉዞ ማድረግ ይችላሉ ብለዋል።
"ለደኅንነት ቅድሚያ እንደሚሰጥ" አየር መንገድ የይለፍ መተግበሪያውን ለመሞከርም የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር መንገድ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
"ይህ መተግበሪያ መንገደኞች በጉዞ ላይ በራስ መተማመን እንዲኖራቸው እንዲሁም አገራት በሙሉ ልብ ድንበሮቻቸውን በድጋሚ እንዲከፍቱ የሚያበረታታ ነው" ሲሉም ሥራ አስፈጻሚው አክለዋል።
የአያታ ምክትል ፕሬዝዳንት ኒክ ካረን አዲሱ የይለፍ መተግበሪያ ተጓዦች በቀላሉ በአንድ መስኮት የሚያስፈልጉ ሒደቶችን በሙሉ እንዲያከናውኑ ይረዳል ብለዋል። ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ አበረታተዋል።
እስካሁን ይህንን መተግበሪያ ከተቀበሉ አየር መንገዶች መካከል የሲንጋፖር አየር መንገድ ቀዳሚ ሆኗል።
ሩዋንዳ፣ ኢትሃድ፣ ኤምሬትስ፣ ስዊስ እና ጃፓንን ጨምሮ የሙከራ ትግበራውን የጀመሩ አየር መንገዶች ከ20 ማለፋቸውን አያታ ይፋ አድርጓል።