የኤርትራ ወታደሮች መውጣት 'ቴክኒካዊና ወታደራዊ ጉዳይ ነው'- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ታትሟል

የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል መውጣትን በተመለከተ የሚቀረው ወታደራዊ እና ቴክኒካዊ ጉዳይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

ሁለቱም አገራት በአመራር ደረጃ የወታደሮቹን መውጣት የተስማሙበት ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ ፤ ቀሪው ቴክኒካዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

አምባሳደር ዲና "የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ በሁለቱም አገራት ስምምነት ተደርሷል" ያሉት ማክሰኞ ዕለት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ይሁን እንጂ ወታደሮቹ ከኢትዮጵያ ግዛት የሚወጡበት ሁኔታ "የቴክኒክ ጉዳይ ነው፤ የወታደራዊ ጉዳይም ነው። እንዴት ይወጣሉ? ምን ያህል ይወጣሉ? በምን ዓይነት ሁኔታ ይወጣሉ? እንዴትስ ይረጋገጣል? የሚሉት ጉዳዮች የቴክኒካዊ ጉዳዮች ናቸው" ያሉት አምባሳደር ዲና በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጡም።

በትግራይ ክልል ስላለው ግጭት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር መወያየታቸው የገለጹት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን "ትግራይ ውስጥ ያሉት የኤርትራ ወታደሮች በፍጥነት እና መረጋገጥ በሚቻል አኳኋን" ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ የኤርትራ እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ እንቅፋት በመሆን ድርሻ አላቸው ብሏል።

አክሎም እነዚሁ አካላት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገውን የሦስትዮሽ ድርድር በቅርቡ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳላት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

አምባሳደር ዲና የሦስትዮሽ ድርድሩ በቅርቡ እንደሚቀጥል ኢትዮጵያ ጽኑ እምነት አላት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረት ካላት አክብሮት አንፃር ድርድሩ በሕብረቱ እንዲቀጥል ፅኑ አቋም እንዳላት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የሆነችው ዲሞክራቲክ ኮንጎ ድርድሩ እንዲጀመር ትሰራለች የሚል እምነት እንዳላትም ተናግረዋል።

ሱዳን እና ግብጽ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ወደ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ለመውሰድ ፍላጎት ቢኖራቸውም በኢትዮጵያ በኩል ግን ተቀባይነት እንደሌለው በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወሳል።

በሌላ በኩል ሦስቱም አገራት ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ የምትሞላ ከሆነ ሱዳን እከስሳለሁ ማለቷን በተመለከተ የተጠየቁት አምባሳደር ዲና "ከዚህ በፊትም ብዙ ነገር ሲባል ቆይቷል፤ ይህንን ግድብ እናፈርሳለን ሲባል ቆይቷል" በማለት "ይህ ጉዳዩ ጊዜው ሲደርስ ቢመለስ ይሻላል" ሲሉ አክለዋል።

በተጨማሪም አምባሳደሩ "ብዙ ጊዜ ለፉከራ መልስ መስጠት ጥሩ አይደለም፤ ለፉከራ መልስ መስጠት ለፉከራው እውቅና መስጠት ነው። ሁለተኛ ደግሞ የማይሆን ጨዋታ ይሆናል ስለዚህ የሚመከር አይደለም፤ የሚሆነውንም መጠበቅ ይሻላል" በማለት ሱዳን እከስሳለሁ ባለችው ላይ መልስ ሰጥተዋል።

ከቀናት በፊት ሱዳን ኢትዮጵያ ግድቡ መሙላት የምትቀጥል ከሆነ ግድቡ ግንባታ ላይ የተሰማራውን የጣልያኑን ሳሊኒ ኩባንያንና የኢትዮጵያ መንግሥትን እከስሳለሁ ማለቷ ይታወሳል።