ኮሮናቫይረስ፡ የደልሂ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከሰተውን የኦክስጂን እጥረት 'አሳፋሪ' ሲል ተቸ

የፎቶው ባለመብት, European Pressphoto Agency
በሕንድ ደልሂ የሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማዕከላዊው መንግሥት በከተማው ያለውን የኦክስጂን እጥረት የያዘበትን መንገድ በይፋ ተችቷል፡፡
አገሪቱ ረቡዕ 2 ሺህ 23 ሰዎች መሞታቸውን በኮቪድ ምክንያት ሪፖርት ሲሆን ይህም በቀን የተመዘገበው ከፍተኛው ቁጥር ሆኗል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ 200 በላይ የሚሆኑት የኦክስጂን እጥረት በገጠማቸው በደልሂ ሆስፒታሎች የተመዘገቡ ናቸው፡፡
ፍርድ ቤቱ በስድስት የግል ሆስፒታሎች ባለቤቶች የቀረበለትን አቤቱታ እየሰማ ይገኛል።
መንግስት የኦክስጂን አቅርቦት ከፋብሪካዎች ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ወደ ሆስፒታሎች እንዲደርስ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
"ይህ አሳፋሪ ነው። መንግሥት በመላ ህንድ የኦክስጂን አቅርቦትን አስመልክቶ ምን እየሰራ እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን። የኦክስጂን አቅርቦቶችን ለማረጋገጥ መለመን፣ መበደር ... መስረቅ ካለበት ይህ የመንግስት ሃላፊነት ነው" ብለዋል ዳኞቹ፡፡
ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ ባይቻልም በመላ አገሪቱ በርካታ ሰዎች ኦክስጅን ሲጠብቁ ህይወታቸው አልፏል፡፡ የህንድ ማህበራዊ ድር አምባዎችም እንዲሁ በኦክስጂን ያስፈልገናል ጥሪ ተሞልተዋል፡፡
በዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ እና በሞሉ ሆስፒታሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ይሰባሰባሉ፡፡ የጤና አገልግሎቶች ችግሩን ለመቋቋም በመታገል ላይ ናቸው፡፡
ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አንዱ የሆነው የምዕራባዊው የማሃራሽትራ ግዛት ባለሥልጣናት የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ ከሐሙስ ምሽት ጀምሮ ተጨማሪ ገደቦችን ጥለዋል፡፡
ግዛቲቱ ቀድሞውኑም በከፊል እገዳ ስር ነበረች።
ማሃራሽትራ በሕንድ የበለፀገች ግዛት ስትሆን የፋይናንስ ማዕከልዋ ሙምባይ የምትገኝበት ነው፡፡ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶም የኮቪድ ስርጭት ማዕከል ሆናለች፡፡
በህንድ በቫይረሱ ከተያዙ ከ 15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከል ሩብ ያህሉ በግዛቲቱ የተመዘገቡ ናቸው፡፡
ማሃራሽትራ ከሌሎች ግዛቶች በበለጠ 67 ሲህ 468 በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን ሪፖርት አድርጋለች። በህንድ ከ 180 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸውን አረጋግጣለች፡፡ የሟቾች ቁጥር ቢጨምርም የሞት ምጣኔው በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ነው፡፡
ህንድ ባለፈው ወር ጥብቅ ባልነበረው የደህንነት ፕሮቶኮሎች፣ በአዲሱ የቫይረሱ ዓይነት እና ሚሊዮኖች በተሳተፉበት የሂንዱዎች ፌስቲቫል ምክንያት ቁጥሩ በከፍተኛ ፍጥነት መጨመሩ ተገልጿል፡፡ በብሄራዊ የቫይሮሎጂ ተቋም እንዳስታወቀው በማሃራሽትራ ከተመረመሩት መካከል 61 በመቶ የሚሆኑት ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
በየደረጃው ምርጫ በሚደረግበት በምዕራብ ቤንጋል ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን ጨምሮ ግዙፍ የምርጫ ስብሰባዎች መካሄዳቸው አልተቋረጠም፡፡
መራጮች ሐሙስ ለ 6ኛ ዙር ምርጫ ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መንግስት ምርጫው እንዲካሄድ ያሳለፈውን ውሳኔውን ተከላክሏል፡፡
ብዙዎች በሀገሪቱ እየዘገየ የመጣው የክትባት እንቅስቃሴ ስርጭቱን ለመግታት ሲባል በፍጥነት መካሄድ አለበት ብለዋል፡፡
በህንድ ከ 130 ሚሊዮን በላይ ክትባቶችን ብትሰጥ የደረሳቸው የጤና ሠራተኞች፣ ተጋላጭ ሠራተኞች እና ከ 45 አመት በላይ የሆኑ እና ማንኛውም በሽታ ያለባቸው ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
ከግንቦት 1 ጀምሮ ደግሞ ከ 18 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ለክትባቱ ብቁ ይሆናሉ፡፡ የአቅርቦት መዘግየት ሂደቱን የበለጠ ሊያዘገየው ይችላል ተብሏል።












