የፌስቡክ ቦርድ በትራምፕ ላይ የተጣለውን እገዳ በተመለከተ የሚሰጠውን ውሳኔ አዘገየ

ታትሟል

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ሊመለሱ የሚችሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ የፌስቡክ ተቆጣጣሪ ቦርድ ውሳኔውን አዘገየ።

ትራምፕ ከፌስቡክ የታገዱት ከካፒቶል ሂል አመፅ በኋላ በጥር ወር ነበር ።

ቦርዱ እንዳስታወቀው መዘግየቱ የተፈጠረው ከዘጠኝ ሺህ በላይ የሚሆኑ የሕግ ምላሾችን ለመመርመር ጊዜ በመውሰዱ ነው።

ቦርዱ ውሳኔውን በቀጣይ አራት ቀናት ውስጥ ይሰጣል ተብሎ ነበር።

ቦርዱ በትዊተር ገጹ በሰጠው መግለጫ "በሚቀጥሉት ሳምንታት" ውሳኔው ይፋ እንደሚሆን አስታውቋል።

ይህ ውሳኔው የበላይ ተቆጣጣሪ ቦርዱ ባለፈው ዓመት ጉዳዮችን መመልከት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ትልቁ ውሳኔ ይሆናል ተብሏል።

ቦርዱ የተቋቋመው ፌስቡክ በሚገጥሙት አስቸጋሪ ወይም አወዛጋቢ የግልግል ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ነው።

በፌስቡክ አለቃ ማርክ ዙከርበርግ የተቋቋመውና 20 አባላት ያሉት ኮሚቴ ብዙውን ጊዜ 'የፌስቡክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት' ተብሎ ይጠራል።

ኮሚቴው ከጋዜጠኞች፣ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ከጠበቆች እና ከምሁራን የተውጣጣ ነው።

ኮሚቴው እስካሁን በዘጠኝ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል።

ትልልቅ ቴክኖሎጂዎች ትራምፕን አግደዋል

የታገደው የትራምፕ አካውንት ብቻ አይደለም። ፌስቡክ እገዳውን በማራዘም "የትራምፕ ድምጾችን" እንዲያካትት በማድረግ የልጃቸውን ሚስት እና የፎክስ ኒውስ ባልደረባዋ ላውራ ትራምፕ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቃለ መጠይቅ ያደረገችበትን ቪዲዮ ከለቀቀች በኋላ እገዳው ደርሷታል።

የአምስት ሰዎች ሞትና ከ100 በላይ የፖሊስ መኮንኖች ላይ ጉዳት ካደረሰው የካፒቶል ሂል አመፅ በኋላ በርካታ ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እርምጃ ወስደዋል። የቀድሞው ፕሬዝዳንት አመጽ በማነሳሳት እና የውሸት መረጃዎችን በማሰራጨት ተከሰው ነበር።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከዩቲዩብ የታገዱ ሲሆን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሱዛን ዎጂሲኪ "እውነተኛው ዓለም ላይ የሚነሳው የአመጽ" ስጋት ሲቀንስ እግዱን ሊያነሳ ይችላል ብለዋል።

ትራምፕ ከትዊተር ላይ ደግሞ በቋሚነት ታግደዋል።

ከክራውድታንግል የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በአሜሪካ ውስጥ በጣም ታዋቂ ከሆኑት የፌስቡክ ጽሁፎች መካከል የትራምፕ ይገኙባቸዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያዎች ያለ ትራምፕ ጥቂት ወራት ያሳለፉ ሲሆን እገዳው ቋሚ ከሆነ ትራምፕ የራሳቸውን የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ለመፍጠር እያሰቡ ነው።

የትራምፕ አማካሪ ጄሰን ሚለር በመጋቢት ወር ለፎክስ ኒውስ እንደገለጹት የቀድሞው የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዚዳንት "የራሳቸውን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ" ይዘው ይመለሳሉ ብሏል።