ሩሲያ 10 የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን በማባረር አፀፋ መለሰች

ታትሟል

ሩሲያ 10 የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ከአገሯ እንዲወጡ ትዕዛዝ የሰጠች ሲሆን ሌሎች ስምንት ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ደግሞ ወደ አገሯ እንዳይገቡ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ማስገባቷ ተገለፀ።

ሩሲያ ይህን ያደረገችው ማክሰኞ ዕለት አሜሪካ ለጣለችባት ማዕቀብ አፀፋዊ ምላሽ ነው።

ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ከታገዱት መካከል የአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ (ኤፍቢአይ) አባላትና የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለሥልጣናት ይገኙበታል።

ዋይት ሐውስ ሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ባለፈው ዓመት በነበረው 'የሶላር ዊንድ' የሳይበር ጠለፋ እና ሌሎች "ጠብ አጫሪ" ድርጊቶች እንዲሁም በ2020 ምርጫ ጣልቃ ገብነቷ ምላሽ እንደሆነ አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ቅራኔ ውስጥ የገቡት ሁለቱ አገራት፤ አሁን ደግሞ ወደ ባሰበት ውጥረት ውስጥ እየገቡ ነው።

ሩሲያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ያስጠጋች ሲሆን፤ የአሜሪካ የጦር መርከቦችም ወደ ጥቁር ባሕር እያመሩ መሆኑን የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስጠንቅቋል።

ባለፈው ወር መንግሥትን በሚተቸው አሌክሲ ናቫንሊይ መመረዝ ምክንያት አሜሪካ ሰባት የሩሲያ ባለሥልጣናትን እና በርካታ የመንግሥት ተቋማትን ኢላማ አድርጋለች።

ሩሲያ ግን በአሌክሲ መመረዝ እጇ እንደሌለበት ገልጻለች።

ሆኖም በዚህ ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ለሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ሁለቱ አገራት አብረው ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸው ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ጥሪ አቅርበዋል።

ሩሲያም ይህንን በበጎ እንደምትመለከተውና እያሰበችበት እንደሆነ ገልጻለች።

ማዕቀቡ የተጣለበት ማነው?

ሩሲያ 10 የአሜሪካ ዲፕሎማቶች አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ጠይቃለች። ከዚህ በተጨማሪም ስምንት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ወደ አገሯ እንዳይገቡ አግዳለች። ከእነዚህም መካከል፡

• የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጀነራል ሜሪክ ጋርላንድ፣

• የአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ ዳሬክተር ክርስቶፈር ውሬይ እና

• የአሜሪካ የውስጥ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሱሳን ራይስ ይገኙበታል።

ከዚህም ባሻገር ፖላንድ አምስት የሩሲያ ባለሥልጣናትን ማባረሯን ተከትሎ አምስት ፖላንዳዊ ዲፕሎማቶች አገሯን ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።

ሩሲያ በ2020 የአሜሪካ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ ጫና ለማሳደር በመሞከሯ እና ሌሎች የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት አሜሪካ 10 የሩሲያ ዲፕሎማቶች ማባረርን ጨምሮ 32 ተቋማትና እና ባለሥልጣናትን ኢላማ አድርጋለች።

የአሜሪካ የገንዘብ ተቋማትም ከሰኔ ወር ጀምሮ በውጭ ምንዛሪ ላይ መሰረት ያደረገ የውጭ ቦንድ ከሩሲያ ከመግዛት ታግደዋል።