‹የፖሊስ አባሉ በጆርጅ ፍሎይድ የተጠቀመው ሃይል ተመጣጣኝ ነው›› ባለሞያ

ዴሪክ ቾቪን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የሃይል አጠቃቀም ባለሞያ የሆኑት ባሪ ብሩድ የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ እየተመለከተ ላለው ችሎት በሰጡት የባለሞያ ምስክርነት የፖሊስ አባሉ ፍሎይድን መሬት ላይ አጣብቀው ለመያዝ የተጠቀሙት ሃይል ‹‹ተመጣጣኝ ነው›› ሲሉ ገለፁ፡፡

የቀድሞው የፖሊስ ባልደረባ የነበሩት እኚሁ ባለሞያ ጆርጅ ፍሎይድን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያበቃው ‹‹ከፍተኛ አደጋ›› የሚያስከትል ስለሆነ ነው ሲሉም ለችሎት ተናግረዋል፡፡

‹‹እኔ የሚሰማኝ የፖሊስ ባልደረባው ዴሪክ ቾቪን ጆርጅ ፍሎይድን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚናፖሊስን የፖሊስ ፖሊሲዎች ተከትለው ተቀባይነት ባለው መልኩ ሃላፊነታቸውን ሲወጡ ነበር›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከፖሊስ ጫማ ውስጥ ሆነን ስንመለከት አንድ ነገር እስኪፈጠር አትጠብቅም፡፡ አንድ ሰው ሊጥልህ፣ ሊወጋህ፣ ሊተኩስህብህ እንደሚችል ምክንያታዊ ፍራቻ ሊኖርህ ይገባል›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አክለውም ‹‹በአንድ ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ የአንድ ፖሊስን ተግባራት መተቸት ቀላል ነው፡፡ በፖሊሱ ጫማ ውስጥ ሆኖ ማሰብ፣ ምን እየተሰማው እንደሆነ፣ ምን እያያ እንደሆነ እና የሚሰማውን ፍርሃት ተመርኩዘው ስለሚወስዱት ቆራጥ የሆነ እርምጃ ማሰብ ግን ቀላል አይደለም›› ብለዋል፡፡

በጠበቃው ‹‹የፖሊስ አባላት የተጠቀሙት ጉልበት የህይወት መጥፋትን የሚያስከትል ነበር ወይ›› ሲል ላቀረቡላቸው ጥያቄም ‹‹አይ፣ አይደለም›› ሲሉ በአጭሩ መልስ ሰጥተዋል፡፡ የፖሊስ አባሉ ጆርጅ ፍሎይደን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚሞክሩበት ወቅት ከባዋቸው የነበሩ ሰዎች ትኩረታቸውን ጆርጅ ፍሎይድ ላይ እንዳያደርጉ አድርጎአቸው ነበር ብለውም ለችሎቱ ገልጸዋል፡፡

አሁን የክስ ሂደታቸው እየታየ የሚገኘው የፖሊስ አባል ዴሪክ ቾቪን ጆርጅ ፍሎይድ የተሰኘውን ጥቁር አሜሪካዊ በቁጥጥር ስራ ለማዋል በአንገቱ ላይ ተንበርክከው ታይተዋል፡፡

ከፍሎይድ ግድያ ጋር ተያይዞም የቀረበባቸውን የሰው ነፍስ የማጥፋት ክስ ክደው ለችሎቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመለው አለም በፍሎይድ አንገት ላይ ተንበርክከው የሚያዩበት እና እርሱም መተንፈስ አልቻልኩም እያለ የሚማፀንበት ቪዲዮ ከተሰራጨ በኋላ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሷል፡፡