አማዞን ላይ የቦምብ ጥቃት ሊፈጽም ነበር የተባለው በቁጥጥር ስር ዋለ

የአውስ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የአሜሪካ ባለስልጣናት የአማዞን መረጃ ማዕከል ውስጥ ቦምብ ሊያፈነዳ ነበር ያሉትን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ተገልጿል።

ግለሰቡ በጥቃቱ 70 በመቶ የሚሆነውን የበይነ መረብ አገልግሎት ለማቋረጥ አስቦ ነበር ተብሏል።

የ28 ዓመቱ ሴዝ ፔንድሊ በቁጥጥር ስር የዋለው የፈንጂ መስሪያ እቃ የሚሸጥ ሰው በመምሰል በቀረበው የኤፍቢአይ የደህንነት አባል ምክንያት ነው። በዚህም ምክንያት ሴዝ ተቀጣጣይ ፈንጂ በመጠቀም ህንጻ ለማፍረስ በማሰብም ክስ ቀርቦበታል።

ኤፍቢአይ በግለሰቡ ላይ ክትትል ማድረግ የጀመረው በበይነ መረብ በኩል የሚለቃቸው ምልዕክቶች ያስፈራው አንድ ግለሰብ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ነው። ሴዝ በተጠረጠረው ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስር ይጠብቀዋል።

መርማሪ ባለስልጣናት እንዳሉት ከሆነ ግለሰቡ በፈንጂው የአማዞንን ዋነኛ ሰርቨር ለማበላሽት ነበር እቅዱ።

ተጠርጣሪው 70 በመቶ የሚሆነውን የበይነ መረብ አገልግሎት ለማቋረጥ ትልቅ ድርሻ አላቸው ያላቸውን 24 ህንጻዎች የመረጠ ሲሆን የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ እና ኤፍቢአይ ጭምር የሚጠቀሙበት ነው።

አማዞን ዌብ ሰርቪስስ በዘመናዊው የበይነ መረብ አገልግሎት ከፍተኛ ሚና ያለው ተቋም ነው። በርካታ የግልና የመንግሥት ድርጅቶች የሚጠቀሟቸው ዌብሳይቶችን መረጃ በማጠራቀምና ደህንነታቸውን በመጠበቅ ላይ ቀላል የማይባል ኃላፊነት አለው።

በነዚህ የመረጃ ማዕከሎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ምናልባት ለሰአታት አልያም ከዚያ በላይ አገልግሎት እንዲቋረጥ የሚያደርግ ሲሆን ጉዳቱ ቀላል የሚባል አይደለም።

ለምሳሌ በአውሮፓውያኑ 2017 ላይ የአሜሪካ መረጃ ማዕከል ችግር አጋጥሞት በርካታ ታዋቂ ድረገፆች ለሰአታት ከአገልግሎት ውጪ ሆነው ነበር።

በሌላ አጋጣሚ ደግሞ አንድ የአውሮፓ መረጃ ማዕከል ላይ ባጋጠመ እክል ምክንያት እስከ 3.6 ሚሊየን የሚደርሱ ድረገጾች መስራት አቁመው ነበር።

''ላደረጉት ምርመራ ኤፍቢአይን ማመስገን እንፈልጋለን። የደንበኞቻችን እና ሰራተኞቻችንን የመረጃ ደህንነት ጉዳይ በጥብቅ የምንከታተለው ነው። ለሰራተኞቻችን እና ለደንበኞቻችን ስንል ይህን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን'' ብለዋል የአማዞን ቃል አቀባይ።

በዋሺንግተን ዲሲ ካፒቶል ሒል ሕንጻ ላይ የትራምፕ ደጋፊዎች የተቃውሞ ግርግር ሲፈጥሩ ተከሳሹ ሴዝ ፔንድሊ በቦታው እንደነበር ደርሼበታለው ብሏል ኤፍቢአይ። አክሎም ምንም እንኳን በቦታው ይገኝ እንጂ ወደ ህንጻው ውስጥ አልገባም ነበር ተብሏል።

ይህ ከሆነ ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በአንድ የሚሊሻ ድረገጽ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ማሰቡን የሚያመላክት መልዕክት ማስተላለፉን አንድ ዜጋ ለኤፍቢአይ ጠቁሟል።

''እንዲህ አይነት መልዕክት ተመልክቶ ወዲያው ለኃላፊዎች ያሳወቀውን ዜጋ በጣም ማመስገን እንፈልጋለን። ይህ ጥቆማ ባይደርሰን ኖሮ ምናልባት በርካታ በቴክኒክ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችል ነበር'' ብለዋል ጊዜያዊ የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፐርራክ ሻህ።

ተጠርጣሪው በድረገጹ ላይ ያስተላለፈውን መልዕክት በመከተል ኤፍቢአይ ባደረገው ተጨማሪ ምርመራ የግል ኢሜል አድራሻውን ማግኝት ችሏል። በመቀጠልም የግለሰቡን ማንነት ካረጋገጠ በኋላ ክትትል ማድረግ ጀምሯል።

በመቀጠል ፈንጂ መስሪያ ቁሳቁሶችን የሚያቀርብ ሰው በመምሰል አንድ የኤፍቢአይ ምልምል ተጠርጣሪዊን እንዲቀርበው ተደርጓል። በመጨረሻም ሴዝ መሳሪኣዎቹን ከግለሰቡ ተቀብሎ ወደ መኪናው ካስገባ በኋላ ሊሄድ ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል።

በአሁኑ ሰአት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር።