ስደተኞችን የያዘች ጀልባ ከጂቡቲ አቅራቢያ ተገልብጣ ቢያንስ 42 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ቢያንስ 42 የሚሆኑ ስደተኞች በጂቡቲ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ሰጥመው መሞታቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት፣ አይኦኤም አስታወቀ።
ስደተኞቹ መነሻቸውን ያደረጉት በጦርነት ከምትናጠው የመን እንደሆነና በጀልባዋ ላይም 60 ስደተኞች ተሳፍረው ነበር ተብሏል።
ጀልባዋ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት የተሳፈሩባት እንደሆነች አይኦኤም በተጨማሪ አስታውቋል።
ጀልባዋ በመገልበጧ ስደተኞቹ ባሕሩ ውስጥ መስጠማቸው የተነገረ ሲሆን ለጀልባዋ አስካሁን ለአደጋው መከሰት የተሰጠ ምክንያት የለም።
መነሻቸውን ከአፍሪካ ቀንድ ያደረጉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች አደገኛና አሰቃቂ በሚባል ሁኔታ የሚደረገውን ጉዞ አቆራርጠው ለተሻለ ህይወት ወደ ገልፍ አገራት ያቀናሉ።
ይህም ሁኔታ የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አይ ኦ ኤም አስታውቋል።
በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ አገራት ድንበራቸውን መዝጋታቸውን ተከትሎ ስደተኞቹ ወደ አገሮቻቸው ሊመለሱ ተገደዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አሰቃቂ በሚባል ሁኔታ በየመን መውጫ አጥተው የሚገኙበት ሁኔታ ላይ ናቸው።
በየመን ያለውን አደገኛ ሁኔታ ለማምለጥም ለህገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ገንዘብ ለመክፈል ተገደዋል።
በባለፈው ወር ቢያንስ 20 የሚሆኑ አፍሪካውያን ስደተኞች በጅቡቲ ባህር ዳርቻ አካባቢ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከጀልባ ላይ ተወርውረው ሕይወታቸው ማለፉን የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል።
የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በበኩሉ አዘዋዋሪዎቹ ጀልባው ከሚገባው በላይ መሙላቱን ሲያስተውሉ "ቢያንስ 80 የሚሆኑትን ስደተኞች ወደ ውሃ ገፍትረዋቸዋል" ብሏል።
ጀልባው 200 የሚሆኑ ስደተኞችን ጭኖ የነበረ ሲሆን ከስደተኞቹ መካከልም ሴቶችና ህጻናት ይገኙ እንደነበር የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል።
አብዛኛዎቹ ስደተኞች ወደ የመን ጉዟቸውን እያደረጉ የነበረ ሲሆን ከየመን ደግሞ ወደ ሳኡዲ አረቢያ በማቅናት የተሻለ ህይወትና ስራ ለማግኝት የሚሞክሩ ናቸው።












