በልዑል ፊሊፕ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አይገኙም ተባለ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ታትሟል

ከቀናት በፊት ህልፈታቸው የተሰማው የኤደንብራው መስፍን ልዑል ፊሊፕ በቀጣዩ ቅዳሜ 30 ሰዎች ብቻ በተገኙበት የቀብር ስርዓታቸው ይከወናል።

ሆኖም ለንጉሳውያን ቤተሰቦች ቦታ ለመልቀቅና "በተቻለ መጠን ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ" ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የስርዓቱ ታዳሚ እንደማይሆኑ ፅህፈት ቤታቸው አስተውቋል።

በቻፕል ዊንድሶር ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚፈፀመው ስርዓተ ቀብር የመስፍኑ ልጆች፣ የልጅ ልጆችና ሌሎች የቅርብ ቤተሰብ አባላት ብቻ መሳተፍ ይችላሉ።

ቀደም ተብሎ ህዝቡ በስርዓቱ ለመታደም እንዳይሞክር ተነግሯል።

በካንተርበሪ ካቴድራል የመስፍኑ የመታሰቢያ መርሃ ግብር ዛሬ ይካሄዳል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በቀጣዩ ሳምንት የሚከወነው ስርዓተ ቀብር እስከዛሬ ከተፈፀሙ የንጉሳውያን ቤተሰብ የቀብር ስርዓት የተለየ ገፀታ ይኖረዋል።

ሆኖም የባኪንግሃም ቤተ መንግስት የቀብሩ ስርዓት "የመስፍኑን ምኞቶች በሚያንፀባርቅ መልኩ" ይካሄዳል ብሏል።

የልዑሉን ህልፈተ ህይወት ተከትሎ በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ መርሃ ግብሮች ደንቡን ለማድረስ እንጂ እንደከዚህ ቀደሞቹ የንጉሳውያን ቤተሰቦች ቀብር ግዙፍ ስርዓቶችን የሚታዩባቸው አይሆንም ተብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ቃል አቀባይ " የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በወጡ መመሪያዎች ምክንያት በኤደንብራው መስፍን ልዑል ፊሊፕ ቀብር ላይ 30 ሰው ብቻ ይገኛል።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለንጉሳውያን ቤተሰብ ይጠቅማል ያሉትን በማሰብና በሳቸው ቦታ ሌላ ንጉሳዊ ቤተሰብ እንዲታደም በቀብር ስርዓቱ አይገኙም።" ሲል ገልጿል።

በቀብር ስርዓቱ በቅርብ ከንጉሳዊ ቤተሰብ ራሱን አግሎ ካሊፎርኒያ የሚኖረው የሰሴክሱ መስፍን ሃሪ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

ነገር ግን ሁለተኛ ልጇን ያረገዘችው የሰሴክሱ ልዑል ሃሪ ባለቤት ሜገን ግን ወደ ዩኬ እንዳትበር በሀኪሟ ምክረ ሃሳብ ቀርቦላታል።

የቀብር ሰርዓቱ በሚፈፀምበት ቀን የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎተ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚደረግም ተመላክቷል።