የምያንማር ሙስሊሞች፡ ኦማር የቤተሰቦቹ ገዳዮች ፍርድ ቤት ቆመው ያይ ይሆን?

ታትሟል

ባንግላዴሽ የሚገኝ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነው የሚኖረው፤ የ11 ዓመቱ ኦማር። ነጋ ጠባ እናትና አባቱን ያስታውሳል።

«ወላጆቼ በጣም ይወዱኝ ነበር። በደንብ ይንከባከቡኝም ነበር።»

ወላጆቹ በምያንማር ወታደሮች የተገደሉት ከሁለት ዓመት በፊት ነበር። አልፎም ሦስቱ ወንድሞቹ እና ሁለት እህቶቹ የምያንማር ወታደሮች ሰለባ ሆነዋል።

«ሁሌም ጠዋት ስነሳ አለቅሳለሁ። ከዚያ እምባዬን ጠርጌ ወደ ትምህርት ቤት እሄዳለሁ።»

በቀደመ አጠራሯ በርማ፤ አሁን ምያንማር በመባል የምትታወቀው ሃገር የሚኖሩ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ የደረሰው በደል ሁለት ዓመት ቢያልፈውም ኦማር እና ወገኖቹ ላይ የደረሰውን ማሰብ አሁንም ከባድ ነው።

የኦማር ታሪክ ተሰምቶም ጥፋተኞች እስካሁን ለፍርድ አልቀረቡም ማለት አይቻልም ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል። የሮሂንጃ አናሳ ሙስሊም ዜጎች ላይ የተፈፀመውን ግፍ አስመልክቶ የተሰየመ ይህ ነው የሚባል ችሎት የለም።

ከሰሞኑ ግን አዲስ ነገር ተሰምቷል። ለሌላው ሰው ተራ ነገር ቢመስልም የሕግ ባለሙያዎች ግን ይህ ትልቅ እመርታ ነው ሲሉ ይደመጣሉ።

የምያንማር የጦር መሪዎች ፍርድ ቤት ያልቆሙት ለምንድነው?

ባለፈው ዓመት መስከረም የተባበሩት መንግሥታት አቃቤ ሕግ የምያንማር ጦር መሪዎች የራካይን ግዛት ነዋሪ የሆኑ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ ለፈፀሙት ወንጀል ፍርድ ቤት ሊቆሙ ይገባል ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት አቃቤ ሕግ ከሆነ 700 ሺህ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ከራካይን ግዛት በግዴታ እንዲለቁ ሆነዋል።

አንዲት ሃገር ውስጥ መሰል ግፍ ሲፈፀም ቀላሉ ነገር ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት መውሰድ ነው። ምክር ቤት ደግሞ ፋይሉን ወደ ዓለም አቀፉ የጦር ፍርድ ቤት [አይሲሲ] ይመራዋል። የዚህ ፍርድ ቤት ሥራ በጦር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለፍርድ ማቅረብ ነው።

ነገር ግን ይህ እንዳይሆን ሁለት ጉዳዮች እንቅፋት ሆነዋል። አንደኛዋ ቻይና ናት፤ ቻይና የምያንማር ቀንደኛ አጋርና ጎረቤት ናት። ያላትን ድምፅ ተጠቅማ ክሱ ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት (አይሲሲ) እንዳይመራ መሻር ትችላለች። ሁለተኛው ደንቃራ ምያንማር የአይሲሲ አባል አገር አለመሆኗ ነው።

ታድያ እንዲህ ከሆነ የሕግ ባለሙያዎቹን ተስፋ ያጫረው ዜና ምንድነው? አንደኛው ዜና አይሲሲ ባንግላዴሽ ድንበር ላይ የተፈፀሙ የጦር ወንጀሎችን መመርመር እጀምራለሁ ማለቱ ነው። ባንግላዴሽ የአይሲሲ አባል መሆኗ ሁኔታውን በአንፃራዊ ቀለል ያለ ያደርገዋል።

አይሲሲ ድንበር ላይ ተፈፀሙ የሚለው ወንጀል የሮሂናጃ ሙስሊሞች ከመንደራቸው እንዲሰደዱ ማድረግ ነው። ዘር ማጥፋትና መሰል የጦር ወንጀሎችን ከድንበር ወዲህ የማየት ሥልጣን የለውም።

የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሃፊ ኮፊ አናን ይመሩት የነበረው ኮሚሽን አባል የሆኑት ላቲታ፤ ፍትህ ብትዘገይም. . . ይላሉ። «ሥልጣን ላይ ከሆንክ ማንም አይነካህም፤ ትጠበቃለህ። ማንም ወደ ሄግ አይልክህም።»

ቢሆንም ይላሉ ዲፕሎማቷ፤ «ቢሆንም የምያንማር የጦር መሪዎች ለዘላለም ከሕግ ጥላ ያመልጣሉ ማለት አይደለም። እነ ሚሎሴቪችን መጥቀስ እንችላለን። ቢዘግይም እንኳ ለፍርድ ቀርበዋል።»

የሳን ሱ ኪ ጉዳይስ

የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋ ሎሬት ኦንግ ሳን ሱ ኪ የምያንማር ሲቪል አስተዳደር መሪ ናቸው። በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት የጦር ሠራዊቱን የማዘዝ መብት የላቸውም። ነገር ግን የሮሂንጃ ሙስሊሞች ሰብዓዊ መብታቸው ሲጣስ መጠበቅ አልቻሉም ተብለው በሰፊው ይወቀሳሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርማሪው ክርስቶፈር ሲዶቲ ጦር ሠራዊቱ የራሱ ኃይል ኖሮት ወንጀል ሲፈፅም የሲቪል መንግሥቱ አቅም ሳይኖረው ቀርቶ ዝም ስላለ ከጥፋት ይድናል ማለት አይደለም ይላሉ።

ሁለተኛው ተስፋ ሰጭ ዜና አርጀንቲና ውስጥ የተከፈተው ፋይል ነው። ክሱ የምያንማር የጦር ሠራዊት መሪዎች ፈፀሙት ተብሎ በተጠረጠሩበት የጦር ወንጀል ይቀጡ ይላል። ከዚያም አልፎ ሳን ሱ ኪን ጨምሮ ሌሎች የሲቪል አስተዳዳሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ይወትውታል።

የአርጀንቲናውን ክስ የመሠሩቱት ታዋቂ የሕግ እና የሰብዓዊ መብት ተማጓች ነን የሚሉ ሰዎች ናቸው። 'ዩኒቨርሳል ጁሪስዲክሽን' የተሰኘውን ማዕቀፍ መሠረት አድርጎ የተከፈተው ክስ ከተሳካ ተከሳሾች የትኛውም አገር ላይ ክሳቸው ሊታይ ይችላል።

የምያንማር መንግሥት የቀረበበትን ክስ አጣጥሏል። ነገር ግን ክሱ ስኬታማ ከሆነ የጦር ወንጀለኞችም ሆኑ ሳን ሱ ኪ ከአገራቸው ውጭ ሊሄዱ የሚችሉት ወደ ወዳጅ አገራት ብቻ ነው።

የሳን ሱ ኪ ስም አወዳደቅ ብዙዎችን ማስደነቁ ግን አልቀረም። ከእስያዋ ማንዴላ ወደ ዓለም አቀፍ ተፈላጊ ወንጀለኛ ማምራቱ ሳይታለም የተፈታ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

አልፎም የበሬ ግንባር የምታክለው ምዕራብ አፍሪካዊት አገር ጋምቢያ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ ወንጀል ተፈፅሟል ስትል ምያንማርን ከሳለች።

በቀጣይ. . .

ሦስቱም ክሶች በሚቀጥለው ወር መታየት ይጀምራሉ። የፍርድ ሂደቱ ምን ያህል ጊዜ ይውሰድ የሚታወቅ ነገር የለም። ረዥም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ግን ይገመታል።

እስከዚያው ግን በምያንማር ራካይን ግዛት የሚገኙ 400 ሺህ ገደማ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ዜግነት አልባ እንደሆኑ ይኖራሉ። በነፃነት መንቀሳቀስ የሚታሰብ አይደለም። ትምህርት እና የጤና አገልግሎት ማግኘት ዘበት ነው።

ባንግላዴሽ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ አንድ ሚሊዮን ገደማ ኦማርን የመሰሉ የሮሂንጃ ሙስሊሞችም ቢሆን ነገ ከነገ በስቲያ የሚያገኙት ፍርድ የለም። ነገር ግን በተስፋ ይጠብቃሉ።

ኦማርም እናትና አባቱን ይናፍቃል። ወንድምና እህቶቹን ያስባል። ልጅነቱን የተቀማው ኦማር. . .