አስትራዜኒካ ክትባት ከሚያስከተለው ጉዳት የሚሰጠው ጥቅም ይበልጣል ተባለ

የአስትራዜኒካ ክትባት ብልቃጥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የአውሮፓ መድኃኒት ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት ለኮቪድ-19 መከላከል አስትራዜኒካ ክትባትን የሚወስዱ ሰዎች በደም መርጋት የመጠቃታቸው እድል እጅጉን አናሳ ነው ሲል ገለፀ።

በአውሮፓ የተከሰቱ በርካታ የደም መርጋቶችን የመረመረው የአውሮፓ መድኃኒቶች ኤጀንሲ፣ ክትባቱ ከሚያስከትለው ጉዳት ይልቅ ጥቅሙ የላቀ ነው ሲል ተናግሯል።

አስትራዜኒካን የወሰዱ ሰዎች በቀጥታ በደም መርጋት ይጠቃሉ የሚለውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ፍንጭ አላገኘሁም ያለው ኤጀንሲው፤ አብዛኞቹ የተመዘገቡት ክስተቶች እድሜያቸው ከ60 በታች በሆኑ ሴቶች ላይ ሲሆን የተወሰኑ ወንዶችም ችግሩ ገጥሟቸዋል ሲል አብራርቷል።

ኤጀንሲው 86 የደም መርጋት የገጠማቸውን ህሙማን ጉዳይ መርምሯል።

የአውሮፓ ሕብረት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የአስትራዜኒካ ክትባት መውሰዳቸው ተገልጿል።

የኤጀንሲው ዳይሬክተር ኤመር ኩክ ዛሬ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ክትባቱን በወሰዱ የተወሰኑ ሰዎች ላይ የታየው አነስተኛ ፕሌትሌት መኖር እና የደም መርጋት መከሰት በጣም ዝቅተኛ ነው በማለት "በሁሉም እድሜ ክልል በሚገኙ ወንድና ሴቶች" ላይ መከሰቱን ገልፀዋል።

አክለውም ለደም መርጋት መከሰት እድሜ፣ ጾታ ወይንም ከዚህ ቀደም የነበረ ከደም መርጋት ጋር የተያያዘ ሕክምና ታሪክ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ እንደሌላቸው አረጋግጠዋል።

"የክትባቱን ደኅንነት የተመለከተው ኮሚቴ አስትራዜኒካ ኮቪድ-19ን በመከላከል ረገድ ያለው ጥቅም ከሚያስከትለው ጉዳት የላቀ መሆኑን አረጋግጧል።"

ኩክ አክለውም ክትባቱ እጅግ ውጤታማ መሆኑን የጽኑ ህሙማንና አልጋ ይዘው የሚታከሙ ሰዎች ቁጥርን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እንደሚያተርፍ ተናግረዋል።

አስትራዜኒካ በደም መርጋት እና በክትባቱ መካከል ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ግንኙነት አለማግኘቱን አስታውቋል።