ኮሮናቫይረስ፡ ጣሊያን የትንሳኤ በዓል በሚከበርባቸው ቀናት ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች

ጭር ያለ ጎዳና

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ጣሊያን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መስፋፋት ለመከላከል የአውሮፓውያኑ የትንሳኤ በዓል በሚከበርባቸው ሦስት ቀናት ውስጥ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለች።

በየቀኑ 20 የሚጠጉ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን እየመዘገበች ያለችው ጣሊያን ሦስተኛውን ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እየተፋለመች ሲሆን፤ ሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ጥብቅ ቁጥጥር በሚደረግበት "ቀይ ቀጠና" ውስጥ እንዲሆኑ አድርጋለች።

የግድ አስፈላጊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች በሙሉ የተከለከሉ ሲሆን በዓሉን የሚያከብሩ ሰዎች ከሦስት ሳይበልጡ በቤታቸው ውስጥ የትንሳኤ በዓል ማዕድን መቋደስ ይችላሉ።

አብያተ ክርስቲያናት ክፍት ሲሆኑ፤ ምዕመናን የጸሎት ሥነ ሥርዓቶችን ለመሳተፍ ከክልላቸው ውጪ እንዳይሄዱ ተነግሯቸዋል።

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ ለወትሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በሚታደሙበት የትንሳኤ በዓል መልዕክት የሚያስተላልፉበት የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ለሁለተኛ ጊዜ ማንም በማይታደምበት ሁኔታ መልካም ምኞታቸውን ያስተላልፋሉ።

የፋሲካ በዓል የሚከበርባቸውን ሦስት ቀናትን ተከትሎ የሚያዚያ ወር እስኪያልቅ ድረስ የጣሊያን ክልሎች ከጥብቅ የክልከላ ደረጃው ቢወጡም የተለያዩ ክልከላዎችን በማድረግ ይቆያሉ ተብሏል።

ጣሊያን ይህን ጥብቅ ክልከላ የጣለችው በርካታ የአውሮፓ አገራት እየጨመረ ያለውን በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ለመቆጣጠር ጥረት በሚያደርጉበትና የመከላከያ ክትባቱ አቅርቦት በዘገየበት ጊዜ ነው።

አስካሁን ጣሊያን ውስጥ ከ110,328 በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለሞት የተዳረጉ ሲሆን 3.6 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎቿ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተጠቁ ምዕራባዊያን አገራት መካከል ቀዳሚ የሆነችው ጣሊያን ከዓመት በኋላ ሦስተኛውን ዙር የወረርሽኙን ግርሻ ለመቆጣጠር ስትል በትንሳኤ በዓል ቀናት ላይ ጥብቅ ክልከላ ጥላለች።

ከሁለት ቀናት በፊት በተደረገ ምርመራ 23,634 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 501 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

አሁን በተጣለው ጥብቅ ክልከላ አስፈላጊ ከሚባሉት መደብሮች ውጪ ያሉት በሙሉ የተዘጉ ሲሆን ምግብ ቤቶች ሰዎች ወደ ቤታቸው ወስደው የሚመገቡትን ምግብ ብቻ እንዲሸጡ ታዝዘዋል።

በተጨማሪም አስፈላጊ ከሚባሉት ውጭ ምንም አይነት ጉዞዎች ተከልክለዋል። በትንሳኤ በዓል ቀናትም ቤተሰቦችና ጓደኛሞች መጠያየቅ የሚችሉት በክልላቸው ካሉት ጋር ብቻ ነው።

ይህንን ጥብቅ ክልከላ ለማስፈጸምም የጣሊያን መንግሥት 70 ሺህ የፖሊስ መኮንኖችን ቁጥጥር እንዲያደርጉ ማሰማራቱንም አስታውቋል።