'መድኃኒት' አግኝቻለሁ ስትል የነበረችው ማደጋስካር ክትባት ለማግኘት ጠየቀች

የማደጋስካር መሪ የኮሮናቫይረስ 'መድኃኒት' ያሉትን ይዘው

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የማደጋስካር መሪ የኮሮናቫይረስ 'መድኃኒት' ያሉትን ይዘው
ታትሟል

ፕሬዝዳንቷ ከተለያዩ እጽዋት በተዘጋጀ ውህድ የኮሮናቫይረስን ማከም ይቻላል ሲሉ የነበረችው ማደጋስካር፣ የበሽታውን መከለከያ ክትባት ለማግኘት ከሚያስችላት ዓለም አቀፍ ጥምረት ውስጥ ገባች።

የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ከጥቂት ወራት በኋላ በሽታውን ለማከም ያስችላል ያለችውን ባሕላዊ መድኃኒት ያስተዋወቀችው ማደጋስካር ክትባት እንደማያስፈልጋት ገልጻ ነበር።

ኮቫክስ የተባለውና ለበርካታ አገራት የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለማቅረብ ከሚሰራው ጥምረት የአገራት ዝርዝር ውስጥ ባለመግባቷ ክትባቱን ሳታገኝ ቆይታለች።

ማዳጋስካር ኮቪድ-ኦርጋኒክስ የተባለውን ባሕላዊ መድኃኒት በፕሬዝዳንቷ አማካይነት ስታስተዋውቅ የቆየች ሲሆን መድኃኒቱ ወደ ሌሎች አገራትም እንደተላከ ተዘግቦ ነበር።

ነገር ግን የመድኃኒቱ ምንነትና ያስገኘውን ውጤት በሚመለከት በጤና ባለሙያዎች የተባለ ነገር የለም።

ማዳጋስካር የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተቀብለው ሕዝባቸውን እየከተቡት ያለውን የወረርሽኙን መከላከያ ክትባት በኮቫክስ በኩል ለማግኘት ጥያቄ አቅርባለች።

የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ፕሮፌሰር ጃን ልዊስ ራኮቶቮ እንዳሉት ክትባቱን ለማግኘት የተለያዩ ደረጃዎችን ማለፍ አለበት ለዚህ ደግሞ ምዝገባን መፈጸም ዋነኛው እርምጃ ነው ሲሉ የክትባት አቅርቦት ጥምረት ከሆነው ኮቫክስ ውስጥ ለመግባት ማዳጋስካር እያደረገች ያለውን ገልጸዋል።

የማደጋስካሩ ፕሬዝደንት አንድሬ ራጆሊን ኮቪድ-19ን ይፈውሳል በማለት ሲያስተዋውቁት የነበረው 'መድኃኒት' በስፋት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

እስካሁን ባለው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሠረት ኮሮናቫይረስን የሚፈውስ ምንም አይነት መድኃኒት የለም።

በማዳጋስካር እስካሁን ከ24 ሺህ 400 በላይ ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው የታወቀ ሲሆን 418 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሰበብ ለሞት ተዳርገዋል።