"ደራርቱ የጀግንነት፣ የድል፣ የጥንካሬ ማሳያ ናት" - ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ

ደራርቱ ቱሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

እሁድ፣ መጋቢት 19 2013 ዓ.ም ለኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በተደረገ የዕውቅናና ምስጋና መርሀ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ "ደራርቱ የጀግንነት የድል የጥንካሬ ማሳያ ናት" ሲሉ ተናግረዋል።

" ደራርቱ አስታራቂ ሰው የምትወድ፣ ድንቅ ኢትዮጵያዊት ናት" በማለት ለእርሷ የተሰጠው እውቅና ሌሎች የደራርቱ ዓይነት ሰዎች ለማፍራት የሚረዳ መሆኑን ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።

በስካይ ላይት በተደረገ በዚህ የእውቅና ፕሮግራም ላይ ከአዲስ አበባ ምክት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተጨማሪ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፣ ታዋቂ አትሌቶች ፣ አርቲስቶችና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚህ የእውቅና ፕሮግራሙ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ሀያት አካባባቢ የሚገኘው የሀያት አደባባይ በስሟ እንደሚመደብ እና አደባባዩን ለማስዋብ ደግሞ 2 ሚሊዮን ብር መመደቡን ተናግረዋል።

ሌላው ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ደራርቱን "የኢትዮጵያ ገጽታ" ብለው የገለጿት ሲሆን፣ ሱሉልታ የአትሌቲክስ መንደር በስሟ እንደሚሰየም ገልፀው፣ በተጨማሪም 5 ሚሊዮን ብር በስጦታ ሰጥተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ከዚህ ቀደም በአዳማ የሚገኘውን ትልቁ አደባባይን በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ መሰየሙን አስታውሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የፕሮግራሙ አዘጋጆች በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም 350 ግራም የወርቅ ኒሻን እንዲሁም የ2021 ሞዴል የሆነች ሌክሰስ ቪ8 መኪና አበርክተውላታል።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ክለብም የክለቡ ከፍተኛ ሽልማት የተባለ ኒሻን አበርክቶላታል።

አትሌት ደራርቱ ቱሉ በተለያዩ ኦሊምፒኮች፣ በአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች፣ በአለም አገር አቋራጭ ውድድሮች፣ በኮንቲኔንታል ካፕ፣ ከ20 አመት በታች የአለም ሻምፒዮና፣ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች፣ በአለም አትሌቲክስ ፋይናል፣ በጎልደን ሊግ፣ በኢንተርናሽናል ማራቶን እና በኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ሻምፒዮናዎች ከ13 በላይ ወርቆች፣ 2 ብሮች፣ 1 ነሃስና 3 ዲፕሎማዎችን ለሃገሯ ማበርከቷ ተገልጿል።

ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተሰማርታ በተለያዩ አካባቢዎች ሆቴልና መዝናኛዎችን ገንብታ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠር ችላለች።

ይህ የእውቅና ፕሮግራምም በአገር አቀፍ ደረጃ በአትሌቲክስ፣ በኢንቨስትመንት፣ በበጎ ተግባርና ሌሎች ዘርፎች ላደረገችው አስተዋጽኦ የተሰጣት መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽነ መረጃ በሌሎች በኦሎምፒክ አለም አትለትኪስ ጎልደን ሊግ እና ሌሎች ውድድሮች በመሳተፍ ከ13 በላይ የወርቅ ሜዳሊያዎች ሁለት ይርና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ አላት።

ደራርቱ በ1984 ዓ.ም ለአፍሪካ ብሎም ለኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ በ10 ሺህ ሜትር በባርሴሎና የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳልያ አግኝታለች።

በአርሲ በቆጂ የተወለደችው ደራርቱ ቱሉ ወደ ስፖርቱ የገባችው ገና በታዳጊነቷ መሆኑን ከዚህ በፊት በሰጠቻቸው ቃለ ምልልሶች ውስጥ ተናግራለች።

ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የሱማሌ እና ኦሮሚያ ክልል ድንበር አካባቢ በነበረው ግጭት ለተፈናቁ ሰዎች እርዳታ በማስተባበር ጉልህ አስተዋጽኦ ነበራት።

በቅርቡ ደግሞ እነ ጃዋር መሐመድ ከ 30 ቀናት በላይ በረሀብ አድማ ላይ ከቆዩ በኋላ፣ አድማቸውን እንዲያቆሙ ካግባቡ ሰዎች መካከል ዋነኛዋ ደራርቱ ናት።

ደራርቱ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በአመራርነት እያገለገለች ሲሆን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈፋሚ አባልነት እያገለገለች ነው።

ከዚህም በተጨማሪ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል፣ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ዞን ምክትል ፕሬዝዳንትነት እያገለገለች ትገኛለች።