ኮሮናቫይረስ፡ ታዳጊ አገራት ክትባት እንዲያመርቱ የቀረበውን ሃሳብ ሀብታም አገራት መቃወማቸው ተነገረ

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ታዳጊ አገራት ክትባት የማምረት አቅማቸውን ለማጎልበት ድጋፍ ለማድረግ የቀረበውን ሃሳብ ሀብታም አገራት እንዳይሳካ እያደረጉ መሆናቸውን የቢቢሲ ኒውስናይት ፕሮግራም ያገኛቸው ሰነዶች አመለከቱ።

በርካታ ደሃ አገራት የዓለም የጤና ድርጅት በክትባት ማምረት በኩል ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም፤ ባለጸጋ አገራት ግን ከዓለም አቀፍ ሕግ በተቃራኒ የደሃ አገራቱ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንዳያገኝ እየገፉት ይገኛሉ።

ይህ መረጃ የተገኘው በዓለም ጤና ድርጅት የተዘጋጀና ሾልኮ ከወጣ በጉዳዩ ላይ ከተዘጋጀ የድርድር ሰነድ ቅጂ ላይ ነው።

ሃሳቡን ከተቃረኑት ባለጸጋ አገራት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ይገኙበታል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ የሰጡት የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ቃል አቀባይ "አለም አቀፍ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ምላሽ ይፈልጋል" በማለት "የኮሮናቫይረስ ክትባትና ህክምና በዓለም ዙሪያ በፍትሃዊነት እንዲዳረስ በሚደረገው ጥረት አገራችን ቀዳሚ ናት" ብለዋል።

ጨምረውም ለታዳጊ አገራት ከአንድ ቢሊየን ብልቃጥ በላይ የኮሮናቫይረስ ክትባት እንዲቀርብ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛውን ገንዘብ ካበረከቱት አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።

በርካታ ባለሙያዎች እንደሚሉት የክትባቶች ፍትሃዊ ክፍፍል ወረርሽኙንና ሞትን በመከላከል በዓለም ዙሪያ ያለውን በሽታውን የመከላከል አቅምን ያጎለብተዋል።

ነገር ግን ዓለም ያላት ክትባቱን የማምረት አቅም ከሚስያስፈልገው አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን ብቻ እንደሆነ የህክምና ፖሊሲና የአእምሯዊ ንብረት ሕግ ባለሙያ የሆኑት ኤለን ቲሆን ይናገራሉ።

"እነዚህ ክትባቶች በሀብታም አገራት ተመርተው በእነሱ ቁጥጥር ስር የሚቆዩ ናቸው። ስለዚህም በማደግ ላይ ያሉ አገራት ክትባቱን ብቻ ሳይሆን ክትባቱን በማምረት በኩል ተገቢው ድርሻ እንዲኖራቸው እየጠየቁ ነው" ብለዋል።

ክትባት ለማምረት በሌሎች በባለቤትነት የተያዙትን የክትባቶችን ግብአቶች የመጠቀም መብት ማግኘት ብቻ በቂ አይደለም፤ ከዚህ በተጨማሪ ክትባቶቹ እንዴት እንደሚሰሩ ዕውቀት ሊኖር ይገባል ምክንያቱም ቴክኖሎጂው ውስብስብ ሊሆን ስለሚችል።

የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ ረገድ የባለቤትነት መብቶችን ችላ ሊላቸው አይችልም። ነገር ግን አገራትን በማግባባት የክትባት አቅርቦት ከፍ እንዲል ለማድረግ እየጣረ ነው።

ውይይቱም ከዓለም አቀፍ ሕጎች አንጻር የባለቤትነት መብትን በተመለከተ መግባባትን በመፍጠር አገራት ቴክኒካዊ አቅም አግኝተው ክትባቶችን እንዲያመርቱ ለማድረግ የሚያስችሉ አማራጮችን በመፈለግ ላይ አተኩረዋል።

ነገር ግን የመድኃኒት ኢንዱስትሪው ይህ የባለቤትነት መብትን የሚሸረሽር እርምጃ ወደፊት ኮቪድንና ሌሎች ህመሞችን ለማከም በሚያስፈልገው ገንዘብ አቅርቦት ላይ የራሱ የሆነ እንቅፋትን ይፈጥራል ሲል ይከራከራል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ የመድኃኒት አምራቾች ተወካዮች ይህንን ስጋታቸውን በሚመለከት ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል።

በደብዳቤያቸው ላይ ለባለቤትነት መብት የሚደረገው ጥበቃን ማንሳት አዲስ የቫይረስ ዝርያዎችን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጨምሮ በወረርሽኙ ዙሪያ የሚደረገውን ጥረት ይጎዳዋል ብለዋል።

ክትባት በስፋት እንዲመረት በቀረበው ሃሳብ ዙሪያ የተለያዩ ተቃራኒ አቋሞች እየተንጸባረቁ ሲሆን ባለጻጋ አገራትም ይህንን ሃሳብ እንደተቃወሙት ቢቢሲ ያገኘው ሾልኮ የወጣ ሰንድ ያመለክታል።