ዶናልድ ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው "ክትባት ብትወስዱ መልካም ነው" አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው አወዛጋቢ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሪፐብሊካን ደጋፊ የሆኑ ሰዎች ክትባት እንዲወስዱ ጥሪ አደረጉ፡፡
ትራምፕ በቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ቃለ ምልልስ ክትባቱ አስተማማኝና ጥሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የዶናልድ ትራምፕ ይህ ምክር ዜና ለመሆን የበቃው ጽንፈኛና አክራሪ ደጋፊዎቻቸው በኮሮና ዙርያ የተዛባ አመለካከት ይዘው መቆየታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
በርካታ የትራምፕ ደጋፊዎች የኮሮና መኖርን የማያምኑ ናቸው፤ ክትባቱም ሌላ ዓላማ አለው ብለው ያስባሉ፡፡
በርካታ የትራምፕ ነጭ አክራሪ ደጋፊዎች ክትባት አንከተብም ሲሉ የሚፎክሩ እንደነበሩ ዘገባዎች አረጋግጠዋል፡፡
ደጋፊዎቻቸው ብቻም ሳይሆን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ራሳቸው በኃላፊነት ሳሉ የኮቪድ ወረርሽኝን ሲያጣጥሉት ነው የኖሩት፡፡ በዚህ የተነሳ የሳቸው በክትባት ዙርያ የሚሰጡት ምክር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አስተሳሰብ የሚቀይር ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡
በአሜሪካ የክትባቱን መጀመር ተከትሎ በሕይወት የሚገኙ ሁሉም የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ስለ ክትባቱ ፈዋሽነት አደባባይ ወጥተው ሰብከዋል፡፡
ነገር ግን ዶናልድ ትራምፕ እስከ ትናንት ድረስ ዝምታን መርጠው ነበር፡፡
ይህም ደጋፊዎቻቸው ክትባት ለመውሰድ አሻፈረኝ እንዲሉ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡
ባለፈው ጥር ትራምፕና ባለቤታቸው ሜላኒያ በነጩ ቤተ መንግሥት ክትባት የወሰዱት በምስጢር ነበር፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር ትናንት ማክሰኞ በነበራቸው ቃለ ምልልስ ‹ክትባቱን ለብዙ ሰዎች እንዲወስዱት አበረታታለሁ፡፡ ለብዙ ደጋፊዎችም በግልጽ የምለው ይህንኑ ነው› ብለዋል፡፡
የቢቢሲ አጋር ሚዲያ የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ በቅርብ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ከሪፐብሊካን ደጋፊዎች አንድ ሦስተኛው ክትባቱን ለመውሰድ የሚያቅማማ ነው፡፡
የዶናልድ ትራምፕ ለክትባቱ በጎ አስተያየት መስጠት የመጣው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በክትባቱ ዙርያ በርካታ ዜጎች በጎ አመለካከት አለመያዛቸው አበሳጭቷቸው ወደ አደባባይ ወጥተው ወቀሳ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው፡፡












