በእንግሊዝ ከእስር የተለቀቁ ሌቦች እንቅስቃሴያቸውን የሚቆጣጠር መሳሪያ ሊገጠምባቸው ነው

ታትሟል

በእንግሊዝ ከእስር የተለቀቁ የታወቁ ሌቦችና ዘራፊዎች እንቅስቃሴያቸውን የሚቆጣጠር ጂፒኤስ ሊገጠምባቸው እንደሆነ ተገልጿል።

እነዚህ ግለሰቦች ዳግም ወንጀል እንዳይፈፅሙ እንቅስቃሴያቸውን ለመቆጣጠር ነው ተብሏል።

ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ ለአስራ ሁለት ወራት ያህልም እያንዳንዷ እንቅስቃሴያቸውን መቆጣጠጠር የሚያስችል ነው ተብሏል መሳሪያው።

በአገሪቷ የፍትህ ሚኒስቴር በበላይነት የሚመራው ይህ ጅማሮ ግዌንት፣ አቮንና ሶምርሴት፣ ዌስት ሚድላንድስና ሌሎች ግዛቶች ካሉ የፖሊስ ኃይሎች ጋር በመጣመር ተፈጻሚ ይሆናል።

ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው የእነዚህን ሰዎች እንቅስቃሴ 24 ሰዓት መከታተል ሊፈፅሙት ካሰቡት ወንጀል እንዲታቀቡ ያደርጋቸዋል።

የመጀመሪያ ሙከራ የሚካሄደው በ250 ጥፋተኞች ሲሆን ለስድስት ወራት ያህልም ውጤታማነቱ የሚታይ ይሆናል ተብሏል።

ፖሊስ የእነዚህን ሰዎች እንቅስቃሴና ሪፖርት የተደረጉ አዳዲስ ዝርፊያዎችን መረጃዎችን በማነፃፀር ጥፋተኞቹ በአካባቢዎቹ ደርሰው እንደሆነ ይገመግማል ተብሏል።

በ30 አመት ውስጥ 12 ጊዜ ተዘርፌያለሁ

ዲያኔ ቲትመስ በባለፈው አመት ታህሳስ ወር ላይ ፀጉር ቤቷ ውስጥ ሌቦች 2 ሺህ ፓውንድ የሚገመት ዋጋ ያለው የፀጉር ማድረቂያ፣ ማለስለሻና ሌሎችንም እቃዎች ዘረፏት።

ኒውፖርት የሚገኘው የቁንጅና ሳሎኗ ሲዘረፍ በ30 አመት ውስጥ 12ኛ ጊዜ ነው።

"ውድ የሚባሉ መሳሪያዎችን ነው የወሰዱት፤ በደንብ አጥንተው እንደመጡ ያስታውቁ ነበር" ብላለች ዲያኔ

"ከአመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ስዘረፍ የገና በዓል በሚከበርበት ወቅት ነበር። ለኛ ደግሞ ገበያው የሚደራበት ወቅት ነው። ምንም የቀራቸው የለም፤ ሙልጭ አድርገው ነው የወሰዱት" ትላለች።

"ጓደኞቼ ጋር ሄጁ የፀጉር ማድረቂያ፣ መቀስ መዋስ ነበረብኝ ያችን ዕለት ያለ ስራ ላለማሳለፍ" በማለት ታስረዳለች።

"በጣም በጣም ነው የተበሳጨሁት። እንዴት አይነት ድፍረት ነው? ሙሉ ህይወቴን ጥሬ ግሬ ነው ይህችን ሳሎን ያቋቋምኳት። ያለምንም ሃሳብ እንዲህ ሰው ሲሰርቅ በጣም ነው የሚያሳዝነው" ትላለች።

ለበርካታ ጊዜያት በመዘረፏ ምክንያት ኢንሹራንስ መጠየቅም አቁማ ነበር። ምክንያቱም ይሔንን ለመሸፈን ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ለኢንሹራንስ መክፈል ስለሚጠበቅባት ነው።

በዚህም ምክንያት የተዘረፈችውን እንደ ኪሳራ እንደምታየውም ትናገራለች። እንዲህ አይነት ጂፒኤስ መሳሪያዎች መምጣታቸው እንደ ዲያኔ ያሉ በርካታ ጊዜ የተዘረፉ ሰዎችን እፎይታ እንደሚሰጣቸው ተዘግቧል።