ኮሮናቫይረስ፡ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የሚወስዱትን የኮቪድ-19 ክትባት እያማረጡ ነው

ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የትኛውን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት እንደሚወስዱ አለመወሰናቸውን ገለፁ።

ኡጋንዳ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባትን ለዜጎቿ መስጠት የጀመረች ቢሆንም ፕሬዝዳነቱ ግን "የትኛውን ክትባት መውሰድ እንዳለብኝ እያሰብኩበት ነው" ብለዋል።

ኡጋንዳ እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ሁሉ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ያመረተውን አስትራዜኒካ ክትባት ለዜጎቿ እየሰጠች ትገኛለች።

ይህ ክትባት የደም መርጋት ያስከትላል በሚል ኔዘርላንድ፣ ቡልጋሪያ፣ ዴንማርክ እና ኖርዌይ የመሳሰሉ የአውሮፓ አገራት እንዳይሰጥ ጊዜያዊ ክልከላ አስቀምጠዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የአስትራዜኔካ ክትባት የደም መርጋትን ስለማስከተሉ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ባለመኖሩ በዚህ ስጋት አገሮች ክትባቱን ከመስጠት መቆጠብ የለባቸውም ብሏል።

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት እሁድ ዕለት በአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው እስካሁን ድረስ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት አለመከተባቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም "ያልተከተብኩበት ቀዳሚው ምክንያት ጥንቁቅ ስለሆንኩ ነው። በዚህ በጽህፈት ቤት አካባቢም ተገቢው ጥንቃቄ ይደረጋል። ሌላኛው ምክንያቴ ግን የትኛውን ክትባት መውሰድ እንዳለብኝ እያማረጥኩ ስለሆነ ነው። ጆንሰን ኤንድ ጆንሰንን ወይስ የቻይናው አልያም የሩሲያውን ልውሰድ የሚለውን አልወሰንኩም።"

የሙሴቪኒ ባለቤት ጃኔት ሙሴቪኒም አለመከተባቸው ታውቋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ጄን አቼንግ ባለፈው ወር የኡጋንዳው ዴይሊ ሞኒተር እና አሜሪካው ዎል ስትሪት ጆርናል የተሰኙ ጋዜጦች ያወጡትን ዘገባ አጣጥለዋል።

ጋዜጦቹ አገሪቱ በይፋ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ሳትቀበል ፕሬዝዳንቱ እና በቅርባቸው ያሉ ሰዎች በድብቅ ተከትበዋል ሲሉ ነበር መረጃውን ይፋ ያደረጉት።

ፕሬዝዳንቱም እሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ ጋዜጦቹ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው ብለዋል።

ጋዜጦቹ "በትልልቅ ፊደል ጽፈው የፊት ገጻቸው ላይ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው፤ አለበለዚያ አንላቀቅም" ብለዋል።

ኡጋንዳ 49.6 በመቶ ዜጎቿን በየደረጃው የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ለመከተብ አቅዳለች።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ 864,000 ክትባቶችን ከኮቫክስ የተቀበለች ሲሆን፣ ተጨማሪ 2,688,000 ክትባቶችን ደግሞ በሰኔ ወር ትቀበላለች ተብሏል።