ኮሮናቫይረስ፡ ትራምፕ ደጋፊዎቻቸውን የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ውሰዱ እንዲሉ ተጠየቁ

ዶ/ር ፋውቺ እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከፍተኛው የሕክምና አማካሪ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎችቸው የኮሮናቫይረስ ክትባትን እንዲወስዱ እንዲያበረታቱ ጠየቁ።

ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ትራምፕ "በሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች ዘንድ በጣም ታዋቂ ነው" በማለት የፕሬዝዳንቱ ቃል የበርካቶችን ሃሳብ እንደሚለውጥ ተናግረዋል።

በቅርቡ በአሜሪካ የተሰራ አንድ ጥናት እንዳመለከተው የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊ ከሆኑ ወንዶች መካከል 49 በመቶዎቹ የኮሮናቫይረስ ክትባትን መውሰድ አይፈልጉም።

ትራምፕ ባለፈው ወር በሪፐብሊካኖች ጉባኤ ላይ ተገኝተው "ሁላችሁም ሂዱና ተከተቡ" ብለው ነበር።

ትራምፕ በይፋ ዜጎች የኮሮናቫይረስን ክትባት እንዲወስዱ ሲያበረታቱ ይህ የመጀመሪያቸው ነው ተብሏል።

ከዚያ በኋላም ምንም ዓይነት አስተያየት ሲሰጡ አልተደመጡም።

ትራምፕ ባለፈው ጥር ወር በግላቸው የኮሮናቫይረስ ክትባትን ወስደዋል።

አራት የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ባራክ ኦባማ፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ፣ ቢል ኪሊንተን፣ እና ጂሚ ካርተር ክትባቱን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀ ቪዲዮ ላይ ታይተዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ወር ሪፐብሊካኖች ባዘጋጁት ጉባዔ ላይ ተገኝተው ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር።

አሜሪካ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ የተጎዳች ስትሆን በጆን ሆፕኪንስ መረጃ መሰረት ከ530 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሲሞቱ 29.5 ሚሊዮን ያህል ደግሞ በተህዋሲው ተይዘዋል።

የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከፍተኛ ጤና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ፋውቺ ፕሬዝዳነት ትራምፕ ወጥተው ለደጋፊዎቻቸው ክትባቱን እንዲወስዱ ቢነግሩ በርካቶች ሊከተቡ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

"በጣም ታዋቂ ሰው ነው። እርሱ ወጥቶ ከተናገረ የማይከተቡበት ምክንያት አይታየኝም" ብለዋል።

ዶ/ር ፋውቺ አክለውም የትራምፕ አስተዳደር "አሁን ያለንን ክትባት እንዲኖረን በማድረግ ረገድ ውጤታማ ሥራ ሰርቷል" ብለዋል።

አክለውም ፕሬዝዳንቱ በስልጣን ዘመናቸው በሰሩት ሥራ ክትባቱ ተገኝቶ አሁን ዜጎች አልከተብም ማለታቸው የሚቃረን መሆኑን ገልፀዋል።

"በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው። ወጥቶ ቢናገር ነገሮችን መቀየር ይችላል" ብለዋል ዶ/ር ፋውቺ።

በአሁኑ ጊዜ ከአምስት አሜሪካውያን መካከል ቢያንስ አንዱ የመጀመሪያውን ክትባት የወሰደ ሲሆን፣ ከዘጠኝ አንዱ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተከትቧል ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት ጆ ባይደን እስከ ሐምሌ 4 ድረስ ዜጎቸቸው ሙሉ በሙሉ ተከትበው እንደሚጨርሱ ያላቸውን እምነት ተናግረው ነበር።